በዩክሬን የሚሳኤል ጥቃቶች በጥቂቱ 60 የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸው ተነገረ
ወታደሮቹ በዶኔስክ ግዛት የሩሲያ ወታደራዊ አዛዥን ለመቀበል ሲጠባበቁ ከኬቭ በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች ተገድለዋል ተብሏል
ሩሲያም ሆነች ዩክሬን ስለጥቃቱ እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም ጥቃቱን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እየወጡ ነው
ዩክሬን በሩሲያ በተያዘችው የቀድሞ ግዛቷ ዶኔስክ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ 60 የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸው ተነገረ።
ትራንስባይከል በተባለው አካባቢ ሜጀር ጄኔራል ኦሌግ ሞይሴይቭ የተባለ ወታደራዊ አዛዥን ለመቀበል ገላጣ ስፍራ ላይ የተሰባሰቡት ወታደሮች በዩክሬን ሁለት ሚሳኤሎች መመታታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከአሜሪካ ሰራሹ ሂማርስ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ የተተኮሱት ሚሳኤሎች በጥቂቱ 60 የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን ከጥቃቱ ከተረፉ ወታደሮች መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፥ ስለጥቃቱ ዝርዝር መረጃን እያሰባሰብኩ ነው ብሏል።
በሚሳኤል ጥቃቱ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ቢሆንም ሩሲያም ሆነች ዩክሬን እስካሁን መግለጫ አልሰጡም።
ጥቃቱ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከመከላከያ ሚኒስትራቸው ሰርጌ ሾጉ ጋር ከመከሩ ከስአታት በኋላ ነው የደረሰው።
ሚኒስትሩ ሀገራቸው አቭዲቭካን ጨምሮ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ድል እየተቀዳጀች እንደሆነ መናገራቸውን ታስ አስነብቧል።
ከሶስት ቀናት በኋላ ሁለት አመት የሚደፍነው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈ ሲነገር ቆይቷል።
ቢቢሲ ራሽያ “ሜዲያዞና” ከተሰኘ ድረገጽ ጋር ያደረጉት ጥናት ግን በጦርነቱ ህይወታቸው ማለፉ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር 45 ሺህ 123 ነው ይላል።
የሀገራቱ መከላከያ ተቋማት የሟቾችን ቁጥር በይፋ ካለማሳወቅ ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር ይገመታል።