ሩሲያ ትናንት ምሽት በሌሎች የዩክሬን ከተሞች ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሰዎች መቁሰላቸውና ህንጻዎች መፈራረሳቸው ተገልጿል
ዩክሬን ከሩሲያ የተተኮሱ 15 ሚሳኤሎችን ማክሸፍ መቻሏን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ጦር ኢታማዦር ሹም ቫለሪ ዛሉዝኒ በቴሌግራም ገጻቸው አሰፈሩት ብሎ ሬውተርስ እንደዘገበው፥ ሩሲያ ወደ ዩኪሬን 18 ሚሳኤሎችን ተኩሳለች።
ከዚህ ውስጥ የዩክሬን የአየር መቃወሚያዎች 15ቱን ምንም ጉዳት ሳያደርሱ እንዲወድሙ አድርጓቸዋል ነው ያሉት ኢታማዦር ሹሙ።
መዲናዋን ኬቭ ኢላማ ያደረጉት የሚሳኤል ጥቃት ሙከራዎች በሶስት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸሙ መሆናቸውም ተገልጿል።
የኬቭ ከተማ አስተዳደር ቀሪዎቹ ሶስት ሚሳኤሎች ያደረሱት ሰብአዊ ጉዳት እና በሰዎች መኖሪያ ላይ የፈጠሩት ውድመት እስካሁን ሪፖርት አልተደረገም ብለዋል።
ሚሳኤሎቹ የት እንደወደቁና ያደረሱት ጉዳትን ከመጥቀስም ተቆጥበዋል።
ከሩሲያ የሚቃጡ የሚሳኤል ጥቃቶች እየጨመሩ መሄዳቸውን ተከትሎ ኬቭ የአየር መቃወሚያ ስርአቷን በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ እያደረገች ነው ተብሏል።
ሩሲያ ትናንት ምሽት ኒፕሮፐትሮቭስክ ከተማ መጠኑ ያልተጠቀሰ ሚሳኤል መተኮሷን ሬውተርስ ዘግቧል።
የድኒፕሮ ክልል መሪዎችም ሰባት የሩሲያን ሚሳኤሎች መተው መጣላቸውንና 25 ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል ነው የተባለው።
በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘው ፓቭሎራድ ከተማም ምሽቱን ሁለት ጊዜ በሚሳኤሎች ተመታ በርካታ ህንጻዎቿ መፈራረሳቸው ተገልጿል።
በሩሲያ የተያዘችውን ዛፓሮዥያ እያስተዳደሩ የሚገኙት ቭላድሚር ሮጎቭም ፓቭሎራድ ላይ ጥቃት የፈጸምነው ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ነው የሚል አስተያየታቸውን በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሩሲያ እየወሰደችው ያለው የሚሳኤል ጥቃት ዩክሬን ለረጅም ጊዜ ስትዘጋጅበት የቆየችውንና በምስራቅ በኩል ልትጀምረው ያሰበችውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመቀልበስ ያለመ ነው ትላለች።