የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የአውሮፓ ሀገራት መከላከያቸውን ለማጠናከር እንዲጣደፉ አድርጓቸዋል ተብሏል
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ በኋላ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በአውሮፓ ከፍተኛ ዓመታዊ የወጪ ወይም ጭማሪ መታየቱ ተነግሯል።
የዓለም ወታደራዊ ወጪ ባለፈው ዓመት በክብረ-ወሰን ማደጉን የግጭት እና የጦር ትጥቅ ጥናት ባለሞያዎች አስታውቀዋል።
የዓለም ወታደራዊ ወጪ በፈረንጆች 2022 በ 3 ነጥብ 7 በመቶ ወይም በ 2 ነጥብ 24 ትሪሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል ሲል የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ለዓመታት እየጨመረ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር የጀመረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የአውሮፓ ሀገራት መከላከያቸውን ለማጠናከር እንዲጣደፉ አድርጓቸዋል ተብሏል።
ሞስኮ "ጠላት እና ጠበኛ" ካለችው የምዕራቡ ዓለም ራሷን ለመከላከል "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ያለችውን እርምጃ ወስዳለች።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ደግሞ ሞስኮ "ግዛትን ለመንጠቅ ያለመ ጦርነት" እያካሄደች ነው ብለዋል።
በዋነኛነት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የአውሮፓ ወታደራዊ ወጪ በ13 በመቶ ጨምሯል ተብሏል።
በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ ሀገራት በውጥረቱ ምክንያት ወታደራዊ በጀቶችን እያሳደጉ እና ለመጠናከር እቅድ ማውጣታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።