ኪየቭ እርምጃው የወጪ ንግዷ ከፍተኛ ጉዳት ይገጥመዋል ብላለች
ዩክሬን የእህል ምርቷ ላይ ገደብ የጣሉባትን ፖላንድ፣ ስሎቫኪያና ሀንጋሪ ለዓለም የንግድ ድርጅት መክሰሷ ተሰምቷል።
ኪየቭ ገደቡ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን የጣሰ ነው ብላለች።
ሦስቱ ሀገራት ዩክሬን ላይ የጣሉት እግድ አርሶአደሮቻቸውን ከርካሽ ምርት ለመጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዋና የንግድ መስመር የሆነውን የጥቁር ባህር ወደብ በመዝጋቱ፤ ኪየቭ የየብስ አማራጭ መስመርን እንድትፈልግ አስገድዶታል።
ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው የእህል ምርት በማዕከላዊ አውሮፓ እንዲዘዋወር አድርጓል ተብሏል።
የማዕከላዊ አውሮፓ ሀገራት አርሶአደሮች ይህን በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል። የዩክሬን እህል ምርቶቻቸውን እያስተጓጎለና ገበያውን እየረበሸ ነው ብለዋል።
ጫናው የበረታበት 27 አባላት ያሉት የአውሮፓ ህብረት ሦስቱ ሀገራትን ጨምሮ በቡልጋሪያና ሮማኒያ ላይ እስከ መስከረም 15 የሚቆይ የእህል ንግድ እግድ ጥሏል።
የእግዱ ቀነ ገደብ ሲያልቅ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እግዱን እንደማያራዝም አስታውቋል።
ይህም የሦስቱን ሀገራት መንግስታት ያስቆጣ ሲሆን፤ ሀገራቱ ህብረቱን አሻፈረኝ በማለት የራሳቸውን እግድ ጥለዋል።
የዩክሬን የኢኮኖሚ ሚንስትር ሀገራት በተናጠል የኪየቭን ምርት ማገድ እንደማይችሉ በእጅጉ ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለዚህም ዩክሬን ሀገራቱን ለዓለም የንግድ ድርጅት ከሳለች ሲሉ ገልጸዋል።
ሀገራቱ በጣሉት እግድ ቀድሞውኑ የተጎዳው የዩክሬን የወጪ ንግድ ከፍተኛ ጉዳት ይገጥመዋል ብለዋል።