የኪየቭ ወታደሮች በሩሲያ መከላከያና በተቀበሩ ፈንጂዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደገጠማቸው ተነግሯል
ዩክሬን በደቡብና ምስራቅ ግንባሮች ወታደሮቿ ተጨማሪ አካባቢዎችን ከሩሲያ ጦር መቆጣጠራቸውን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ምክትል የመከላከል ሚንስትር ሀና ማሊያር በምስራቅ ግንባር ለወራት ከፍተኛ ፍልሚያ ሲደረግባት በነበረችው ባክሙት ከተማ ኪየቭ ሁለት ስኩየር ኪ.ሜ መሬት በቁጥጥር ስር አውላለች ብለዋል።
አክለውም የዩክሬን ጦር ባለፉት ሳምንታት በደቡብ 4.8 ስኩየር ኪ.ሜ መቆጣጠሩን ገልጸዋል።
ምክትል የመከላከል ሚንስትሯ በደቡብና ምስራቅ ግንባሮች ኪየቭ ድል እየቀናትና እየገሰገሰች መሆኑን የሚያመላክትላቸውን አካባቢዎች እየጠቀሱ አብራርተዋል።
በሰኔ ወር ከተጀመረው የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ወዲህ በባክሙት 49 ስኩየር ኪ.ሜ መያዟ ተነግሯል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ኪየቭ ከመልሶ ማጥቃቱ በኋላ በርካታ መንደሮችንና አካባቢዎችን ተቆጣጥሬያለሁ ብላለች።
ሆኖም ወታደሮቿ በሩሲያ መከላከያና በተቀበሩ ፈንጂዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደገጠማቸው ዘገባው ጠቅሷል።
ሮይተርስ ዩክሬን ተቆጣጠርኩ ያለቻቸውን አካባቢ ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
ሩሱያ በኪየቭ የሚታወጁ ድሎች ላይ አስተያየት እምብዛም አትሰጥም።