ከነሄሊኮፕተሩ ወደ ዩክሬን በመግባት የከዳው ሩሲያዊ የ500 ሺህ ዶላር ሽልማት ሊሰጠው ነው
የዩክሬን ደህንነቶች አብራሪውን ከሀገሩ ለማስወጣት ስድስት ወራት የፈጀ ኦፕሬሽን ማካሄዳቸው ተገልጿል
ኬቭ ከሩሲያ ከነጦር መሳሪያቸው ከድተው ለሚገቡ ወታደሮች እስከ 1 ሚሊየን ዶላር መሸለም የሚያስችል ህግ አውጥታለች
ከሁለት ሳምንት በፊት “ኤም አይ- 8” ሄሊኮፕተር እያበረረ ዩክሬን የገባው የ28 አመቱ ሩሲያዊ የ500 ሺህ ዶላር ጉርሻ ተዘጋጅቶለታል ተባለ።
የዩክሬን ወታደራዊ ደህንነት ቢሮ ቃልአቀባይ አንድሪ ዩሶቭ ሌሎች የሩሲያ አብራሪዎችም ከዩክሬን ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ማክሲም ኩርሚኖቭ የተባለው አብራሪ ከዩክሬን የደህንነት ሰዎች ጋር ተነጋግሮ ነው ሀገሩን ከድቶ የወጣው።
ስድስት ወራት ፈጅቷል የተባለው ኦፕሬሽን ኩርሚኖቭ ከሁለት ሳምንት በፊት ካርኪቭ በተባለችው የዩክሬን ምስራቃዊ ከተማ ሲያርፍ ተጠናቋል።
ከአብራሪው ጋር ምን እየተካሄደ እንደሆነ ያላወቁ ሁለት ባልደረቦቹ የነበሩ ሲሆን፥ ሀገራችን አንከዳም በማለታቸው መገደላቸው ተገልጿል።
የኩርሚኖቭ ቤተሰቦች ግን ቀደም ብለው ወደ ዩክሬን እንዲገቡ መደረጉን ነው የዩክሬን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ የሚገኙት።
የከዳው ሩሲያዊ አብራሪ የሚያበራት “ኤም አይ- 8” ሄሊኮፕተር ለሩሲያ ተዋጊ ጄቶች መለዋወጫ እቃዎችን ጭና ነበር ተብሏል።
የዩክሬን ወታደራዊ ደህንነት ማክሲም ኩርሚኖቭ በዩክሬን ሲያርፍ እና እጅ ሲሰጥ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
በቪዲዮው ላይ አብራሪው ሩሲያውያን የሙያ አጋሮቹ የእርሱን ፈለግ እንዲከተሉ ሲጠይቅ ይደመጣል እንደ ሲኤንኤን ዘገባ።
ኬቭ እንደ ኩርሚኖቭ አይነት ውድ ዋጋ ያላቸውን ሄሊኮፕተሮች ይዞ ወደ ሀገሪቱ ለሚገባ የሩሲያ አብራሪ እስከ 1 ሚሊየን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ብላለች።
ሩሲያውያን ወታደሮች ከድተው ወደ ሀገሪቱ ሲገቡ የሚከፈላቸውን የገንዘብ መጠን የሚጠቅስ ህግም ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ ማውጣቷ ይታወሳል።
ለአብነትም የሩሲያን ታንክ ይዞ ወደ ዩክሬን ገብቶ የከዳ ወታደር 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ይሸለማል ይላል ህጉ።
የ28 አመቱ ማክሲም ኩርሚኖቭም ሩሲያን ከድቶ ወደ ዩክሬን በመግባት የመጀመሪያውን ሽልማት ያገኛል ተብሏል።
ሩሲያ እስካሁን ስለአብራሪው የመክዳት ዜና ምንም ምላሽ አልሰጠችም።