ወታደሮቹ ከሴቨሮዶኔስክ ነው እንዲያፈገፍጉ የታዘዙት
ዩክሬን ወታደሮቿ ከሴቨሮዶኔስክ እንዲያፈገፍጉ አዘዘች፡፡
ኪቭ ወታደሮቿ ከሴቨሮዶኔስክ እንዲያፈገፍጉ ያዘዘችው ከተማዋ ምስራቃዊ ዩክሬንን ለመቆጣጠር በሚያስችል ከባድ ዘመቻ ላይ በሚገኘው የሩሲያ ጦር መከበቧን ተከትሎ ነው፡፡
የአካባቢው አስተዳዳሪ የዩክሬን ወታደሮች አሳልፎ ላለመስጠት በሚል ወደ ፍርስራሽነት በተቀየረችው ከተማ እና በአካባቢው የመቆየታቸው ጉዳይ ትርጉም አልባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የሴቬሮዶኔስክ በሩሲያ ወታደሮች እጅ መውደቅ ምስራቃዊ ዩክሬንን በተለይም ሉሃንስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ በእጇ ለማስገባቷ መንገድ የሚጠርግ ነው፡፡ ከሴቬሮዶኔስክ ባሻገር የሚገኘው ሊሲሻንስክ ከተማ ብቻ ይሆናል በዩክሬናውያን ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚቀረው፡፡
ሆኖም የሩሲያ ወታደሮች አሁንም ወደ ሊሲሻንስክ ከተማ እየተጠጉ መሆኑን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ዘመቻው ኪቭን ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ መሄድ አለመቻሉን ተከትሎ ፊቷን ወደ ምስራቃዊ ዩክሬን ካዞረች ሰነባብታለች፡፡ ሰፊውን የዶንባስ ግዛት በመቆጣጠር የሉሃንስክ እና ዶኔስክ አካባቢዎችን ነጻ አውጥቶ በአፍቃረ ሩሲያውያን እንዲያዝ ለማድረግ የሚያስችላትን ዘመቻም ነበር የጀመረችው፡፡ ዘመቻው የተሳካላት እንደሚመስልም ይነገራል፡፡
ሴቬሮዶኔስክ በአካባቢው ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ በኢንዱስትሪ መናኸሪያነቷም ትጠቀሳለች፡፡ ሴቬሮዶኔስክን መቆጣጠር ማለት ለድል እንደመቃረብ ነው የሚባለው፡፡
ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችላትን ዘመቻ አጠናክራ መቀጠሏን ተከትሎም የዩክሬን ወታደሮች እንዲያፈገፍጉ መታዘዛቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡ አፈግፍገው ስለመውጣታቸው የታወቀ ነገር ባይኖርም፡፡
አንዳንድ የውጭ ብዙሃን መገናኛዎች ግን ወታደሮቹ የኢንዱስትሪ ተቋማትን ብቻ ወደ መጠበቁ ማተኮራቸውን ዘግበዋል፡፡