ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምትሰነዝረው ጥቃት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስታወቀች
የሩሲያ ሚሳየሎች በዲኒፕሮፔትሮቭስክ ግዛት የሚገኘውን የዩክሬን ወታደራዊ ማዘዣ ማእከል ማውደማቸውም ተገልጿል
ሩሲያ “ዶንባስን ነጻ አወጣለሁ” በሚል አብዛኛውን ኃይሏን በምስራቃዊ ዩክሬን ማከማቸቷ ይታወቃል
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በሲቪዬሮዶኔትስክ ላይ የምታደርገው ጥቃት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስታወቀች፡፡
የሩሲያ ኃይሎች ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ጥቃት ከከተማዋ ወጣ ብሎ የሚገኘውን ወረዳ ለመቆጣጠር እንደቻሉም
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ "በሲቪዬሮዶኔትስክ አቅጣጫ ያለው ጥቃት በተሳካ ሁኔታ እያደገ ነው" ብለዋል ።
በከተማው ምስራቃዊ ዳርቻ ላይ የሚገኘው የሜትዮልኪን ሰፈራ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቱም ተናግረዋል ።
"የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ግዛት ላይ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታታቸው ቀጥለዋል" ሲሉም አክለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ኮናሼንኮቭ ፤ የሩሲያ ኃይሎች ረዥም ርቀት በሚምዘገዘጉ የካሊብር ክራይዝ ሚሳዔሎች ፤ በዲኒፕሮፔትሮቭስክ ግዛት የሚገኘውን የዩክሬን ወታደራዊ ማዘዣ ማእከል መምታታቸውንና በዚህም የዩክሬይን ጄኔራሎችን እና መኮንኖችን መግደላቸው አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ይበሉ እንጅ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ አደረስኩት ስላለችው ጥቃት ዝርዝር መረጃ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ሮይተርስ በዘገባው አመላክቷል፡፡
ሩሲያ በሴቪዬሮዶኔትስክ ከተማ በሚገኝ የኬሚካል ፋብሪካ ውስጥ የመሸጉ የዩክሬን ሃይሎች መሳሪያ እንዲያወርዱ ከቀናት በፊት ጥሪ ማቅረቧ የሚታወስ ነው፡፡
የሩሲያ የእጅ ስጡ ጥሪ በምስራቃዊ ዩክሬንን ለመቆጣጠር በሚደረገው ውጊያ ላይ ያላትን አቅም ለማሳየት ነው ተብሏል፡፡
ዩክሬን የምዕራባውያን ከባድ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲጨምር እየጠየቀች ነው፤ ሩሲያ ዶንባስን ነጻ አወጣለሁ በሚል አቅዷ ምክንያት አብዛኛውን ኃይሏን በምስራቃዊ ዶምባስ ግዛት ላይ ማከማቸቷም የሚታወቅ ነው፡፡