የአውሮፓ ህብረት ዩክሬን የህብረቱ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ደገፈ
ጥያቄው በመጪው ሳምንት በብራሰልስ በሚደረገው የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ጉባዔ እንደሚወሰን ተገልጿል
ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን የዩክሬንን ጥያቄ ደግፈዋል ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት ዩክሬን የህብረቱ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ደገፈ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ዩክሬን አባል ሆና ቀጣናዊውን ተቋም መቀላቀሏን ደግፏል፡፡ ጥያቄው በመጪው ሳምንት በቤልጂዬም ብራሰልስ በሚደረገው የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ጉባዔ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡
ዩክሬን የህበረቱ አባል ለመሆን መጠየቅ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ አሁንም የህብረቱን 27 አባል ሃገራት ድጋፍ ካገኘች በ28ኛ አባልነት የምትቀላቀል ይሆናል፡፡
በህብረቱ የገዘፈ ተጽዕኖ ያላቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን የዩክሬንን ጥያቄ መደገፋቸው ነው የተነገረው፡፡
ትናንት ወደ ኪቭ አቅንተው የነበሩት የሃገራቱ መሪዎች ለፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጥያቄውን ለመደገፍ ቃል መግባታቸውም ተነግሯል፡፡
ዛሬ አርብ በጉዳዩ ላይ መግለጫን የሰጡት የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደ ለየን የህብረቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አካል ጥያቄውን ያለማቅማማት መደገፉን ገልጸዋል፡፡
ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ዙሪያ ያጠመደችውን ፈንጂ እንድታጸዳ የአፍሪካ ህብረት ጠየቀ
ለየን የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ መለያ የሆኑ ቀለማትን የሚመስል ኮት ለብሰው ነበር መግለጫውን የሰጡት፡፡ ይህም ለዩክሬን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በማሰብ የተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ዩክናውያን አውሮፓዊ መልክ ላለው ዓላማ ለመሞት መዘጋጀታቸውን ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሚሽን ፕሬዝዳንቷ ለጋራ የአውሮፓ ህልማችን አብረን እንድንኖር እንፈልጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ወዲያውኑ ነው ድጋፉን በጸጋ መቀበላቸውን ያስታወቁት፡፡ የህብረቱ አባል ለመሆን በምናደርገው ጥረት ላይ የተመዘገበ የመጀመሪያው የድል መቃረቢያ ሲሉም ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡
ታሪካዊ ላሉት ውሳኔ ቮንደ ለየንን አመስግነው ከቀጣይ ሳምንቱ የመሪዎች ጉባዔ መልካም ውጤትን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡