ዩክሬን በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ማባረሯን ቀጥላለች
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ፥ የመንግስት ተቋማትን ከሙስኞች ነጻ የማድረጉ ስራ ይቀጥላል ብለዋል
ዩክሬን 27 አባል ሀገራት ያሉትን የአውሮፓ ህብረት ለመቀላቀል ሰፊ የጸረ ሙስና ትግል እንድታደግ በህብረቱ ተጠይቃለች
ዩክሬን በሙስና የጠረጠረቻቸውን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ማባረሯን ቀጥላለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ዘብ ምክትል አዛዡ ሩስላን ዙይባ በፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ባለፉት ሳምንታት በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያሰነበተችው ኬቭ፥ የመንግስት ተቋማትን ከሙስና ነጻ የማድረግ ትግሉ ይቀጥላል ብላለች።
የፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ጽህፈት ቤት ባወጣው ድንጋጌ ብሄራዊ ዘብ ምክትል አዛዡ ሩስላን ዙይባ ከሃላፊነታቸው የተነሱበትን ምክንያት ግን አልጠቀሰም።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪም በሰጡት መግለጫም የዙይባን ስም ባይጠቅሱም በመከላከያ ሚኒስቴር እና በህግ አስፈጻሚ ተቋማት የሚታየውን ስር የሰደደ ህገወጥ ድርጊት ለማስቆም ያለመው ዘመቻ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
“የስራ ሃላፊዎቹን የማሰናበቱ እርምጃ የአንድ ሰሞን ጉዳይ አይደለም፤ የመንግስት ተቋማትን የማዘመን እና ከብልሹ አሰራሮች የማጽዳት ትግሉ ይቀጥላል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው አመት አደረኩት ባለው የኦዲት ስራ በብልሹ ተግባር ውስጥ የተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሚኒስቴሩ ሰራተኞች እና ወታደሮች ላይ ቅጣት ማስተላለፉን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ለሙሰኞች ምንም አይነት ምህረት እንደሌለውም ነው የገለጸው።
ዩክሬን ከሩስያ ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች በሙስና ተዘፍቀዋል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ኬቭ የጸረ ሙስና ዘመቻ መጀመሯ የሚታወስ ነው።
በደርዘን የሚቆጠሩ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎችም በቅርቡ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም።
ዩክሬን ከፍተኛ ሙስና የሚታይባት እና የመንግስት መዋቅሯም በዚሁ ችግር የሚፈተንባት ሀገር መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያሳየው፥ ኬቭ በ2021 ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ 180 ሀገራት 122ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የአውሮፓ ህብረት ባለፈው አመት ዩክሬንን በእጩ አባልነት ሲመዘግባት ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የጸረ ሙስና የሪፎርም ስራዎች በትኩረት ልትሰራ ይገባል የሚለው አንዱ መሆኑ ይታወሳል።