የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ ዩክሬንን ጎብኝተው ነበር
ጀርመን፤ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን አዲስ የጦር መሳሪያ ልታበረክት መሆኑን የሀገሪቱ መራሄ መንግስት አስታወቁ።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ፤ ለዩክሬን የሚበረከተው አዲሱ የጦር መሳሪያ በቅርቡ እንደሚላክላት ተናግረዋል። አዲሱ የጦር መሳሪያ “ሱፐር ሞዴል ዊፐን” በመባል እንደሚጠራም ነው መራሄ መንግስቱ የተናገሩት።
መራሄ መንግስቱ ትልቅ የአየር መከላከያ ስርዓት፤ ራዳር እና ድሮኖች ለዩክሬን እንደሚላኩ አረጋግጠዋል።
በዚህም መሰረት ኪቭ በቅርቡ ከጀርመን የሚላኩላትን የጦር መሳሪያዎች እንደምትቀበል ተናግረዋል። መራሄ መንግስቱ፤ በፕራግ በሚገኘው የቻርለስ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር ነው በርሊን ለኪቭ የመሳሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ ያስታወቁት።
ጀርመን በቀጣይ ለዩክሬን ሁሉንም አይነት ድጋፍ እንደምታደርግ መራሄ መንግስቱ አረጋግጠዋል፡፡ በርሊን፤ ኪቭ የፈለገችውን ማንኛውም አይነት ትብብር እንደምታደርግላት መራሄ መንግስቱ ቃል ገብተዋል።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሃምሌ ላይ በዩክሬን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሀገራቸው ዩክሬንን ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በገልጸውላቸዋል።
ዩከሬን እና ሩሲያ ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጀርመንም ለዩክሬን ጦር መሳሪያ ለማቅረብ በሚል ፖሊሲ እስከ ማሻሻል ደርሳ እንደነበረ ይታወሳል።
ሩሲያም በተለያዩ ጊዜያት ከምእራባውያን ለዩክሬን ያበረከቷቸው የረጅም ርቀት ሮኬትን ጨምሮ ይለያዩ የጦር መሳሪያዎችን አወደምኩ ማለቷ አይዘነጋም።