አሽራፍ ሱሊማን ክብረወሰን የያዘበት ቪዲዮ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ተለቋል
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ከትናንት በስቲያ በኢንስታግራም ገጹ ያጋራው የቪዲዮ ምስል መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።
ጸጉር የሚያቆመው ቪዲዮ ረጅም የጭነት ተሽከርካሪን በጥርሱ የሚጎትት ግለሰብን ያሳያል።
አስገራሚውና በርካቶችን መሳቀቅ ውስጥ የሚከተው ቪዲዮ አዲስ ክብረወሰን የያዘውን አሽራፍ ማህሩስ ሞሃመድ ሱሊማን ለአለም ያስተዋወቀ ሆኗል።
አሽራፍ ሱሊማን 15 ሺህ 730 ኪሎግራም የሚመዝን ተሽከርካሪን ነው በጥርሱ ሲጎትት የሚታየው።
- 10 ሺህ ሲኒ ቡና የተጠጣበት “ታላቁ የቡና ቅመሱ ስነ ስርዓት” አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዘገበ
- የአረብ ኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ደማቅ የአዲስ አመት አቀባበል ክብረወሰን ሰብሯል
ግለሰቡ ከጥርሱ ጋር በተያያዘ ገመድ ዳገታማ በሚመስል የአስፋልት መንገድ ረጅሙን የጭነት ተሽከርካሪ ሲጎትት በዙሪያው በርካቶች ድጋፋቸውን ችረውታል።
በደቡብ ምስራቃዊ ግብጽ ኢስማኤላ ከተማ የራሱን ምርጥ ክብረወሰን ለማሻሻል ሙከራ ያደረገው ሱሊማን፥ አዲስ ክብረወሰንን ማሳካት ችሏል።
በጥርስ ከባድ ተሽከርካሪን የመጎተት ክብረወሰኑ በፈረንጆቹ ሰኔ 13 2021 የተመዘገበ ቢሆንም፥ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ከትናንት በስቲያ ነው አስገራሚውን ቪዲዮ የለቀቀው።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ኢንስታግራም ላይ የተለቀቀውን ቪዲዮ የተመለከቱት ሲሆን በርካቶች የግርምት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
አንድ አስተያየት ሰጪ“ሱሊማን የአለማችን ምርጥ የጥርስ ሃኪም ከጎኑ መሆናቸው ግድ ነው” ብሏል።
ሌላኛው ደግሞ “ጥርሱ ከእኔ እጅ በእጅጉ ይጠነክራል” ያለ ሲሆን፥ የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ መስራት ያለበት ሱሊማን ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
የየእለት የጥርስ ጤና አጠባበቅ ልምዱን እንዲያጋራቸው የጠየቁም በርካቶች ናቸው።
በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በጸጉሯ አውቶብስ የጎተተችው አሻ ራኒም እንደ ሱሊማን ሁሉ መነጋገሪያ እንደነበረች ኤን ዲ ቲቪ አስታውሷል።