ትምህርት ቤቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ ተመድ አስጠነቀቀ
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በዓለማችን ከ13 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በጦርነት ወድመዋል
በኢትዮጵያም በአትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የተገነባውን ጨምሮ በርካታ ትምህርት ቤቶች በህወሓት ጥቃት ወድሟል መባሉ ይታወሳል
ትምህርት ቤቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠነቀቀ።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ትምህርት ቤቶች ከማንኛውም ጥቃት ሊጠበቁ ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በአንድነት ትምህርት ቤቶች ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠበቁ ድምጽ እንዲሆን የጠየቁት ዋና ጸሀፊው ትምህርት ቤቶች የነጻነት እና የሰላም ቦታዎች መሆን አለባቸው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ የሚመክር ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ ሊደረግ እንደሚገባ ዋና ጸሃፊው መናገራቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በዓለማችን ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2020 ዓመት ድረስም ከ13 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በተሰነዘሩ ወታደራዊ ጥቃቶች መውደማቸው ተገልጿል።
እንደ ዋና ጸሃፊው ገለጻ ከሆነ በትምህርት ቤቶች ላይ በየጊዜው እየተፈጸሙ ያሉ አደጋዎች እየጨመሩ የመጡ ሲሆን፤ ጉዳዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናትን ቀጣይ ህይወት የሚያመሰቃቅል ድርጊት መሆኑን አክለዋል።
“የትምህርት ቤቶች ደህንነት አዋጅ” የተሰኘው በመንግስታቱ ድርጅት የተረቀቀውን ዓለም አቀፍ ህግ እስካሁን ያጸደቁት 111 ሀገራት ብቻ ሲሆኑ፤ ተጨማሪ የተመድ አባል ሀገራት አዋጁን በበገራቸው ህግ አውጪ ምክር ቤት አጸድቀው የትምህርት ቤቶችን ደህንነት እንዲያስከብሩ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትም ሊቀጡ እንደሚገባም አዋና ጸሀፊው አስጠንቅቀዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ትምህርት ቤቶች የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በቅርቡ በአማራ ክልል ዋግኸህራ ዞን በአትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የተገነባው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በህወሀት ታጣቂዎች እንደወደመ አትሌቱ ማነገሩ ይታወሳል።