“ከሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች የወጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የት እንዳሉ ማረጋገጥ አልቻልኩም” - ተመድ
ኤጀንሲው “ከመጠለያ ጣቢያዎች የሚወጡ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያም ይመለሱ ወዴት የስደተኛነታቸውን ደረጃ እንደሚያጡ”ም ገልጿል
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ “ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር መጠነኛ ቅናሽ” ማሳየቱን አስታውቋል
ከመጠለያ ጣቢያዎች የወጡ ስደተኛች ቢኖሩም የት እንዳሉ ማረጋገጥ እንዳልቻለ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ “የስደተኞች መታወቂያ ይዘው ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ሲሳተፉ የተገኙ ታጣቂዎች አሉ” መባሉን ተከትሎ ትናንት አመሻሽ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ከሰሞኑ “በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩና የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መታወቂያን የያዙ ታጣቂዎች ተገኙ” የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩና በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ሲዘገቡ መመልከቱን ገልጿል፡፡
ለደህንነት ሲባል “የግለሰቦች ጉዳዮችና መረጃ ይፋ ለማድረግ እቸገራለሁ” ያለው ኤጀንሲው “የተመዘገቡት ስደተኞች ሁሉ በመጠለያ ጣቢያው መኖራቸውንና አለመኖራቸውን “የማጣራት ስራ” ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
በማጣሪያው “ከቅርብ ወራት ወዲህ በመጠለያ ጣቢያዎች መጠነኛ የሆነ የስደተኞች ቁጥር መቀነስ መኖሩን” መኖሩን ነው ያመለከተው፡፡
ሆኖም “ከመጠለያ ጣቢያዎች የወጡት ስደተኞች የት እንዳሉ ለማረጋገጥ አልቻልኩም” ብሏል፡፡
ኤጀንሲው የስደተኞች ሁኔታ “በትጥቅ ትግል በንቃት ከመሳተፍ ጋር አይገናኝም፤ አይፈቀድም”ም ሲል ያስታወቀም ሲሆን “ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱም ይሁን ወደ ትጥቅ ትግል የተቀላቀሉ ካሉ” ስደተኝነታቸውን እንደሚያጡ ገልጿል፡፡
በቅርቡ ጉዳዩን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ላቀረበላቸው ጥያቄ የኢ-ሜይል ምላሽ የሰጡት በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች “በቅርቡወደ ኢትዮጵያ በስደተኞች የተደረገ እንቅስቃሴ” አለመኖሩን ገልጸው ነበር፡፡
“በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ሆነን የስደት ተመላሾችን የምናረጋግጥበት ሁኔታም የለም”ም ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ኤጀንሲው “የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሲቪል ባህርይን ጠብቀው እንዲቆዩ እና ይህንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ ለሱዳን መንግስት ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት” ደጋግሞ መግለጹንም ተናግረዋል፡፡
የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ በቅርቡ ወደ ሱዳን አቅንተው መጠለያ ጣቢያዎቹን ጎብኝተው ነበር፡፡
ግራንዴ በዚሁ ጉብኝታቸው ይህንኑ መግለጻቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡
ክሬቨንኮቪች “በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ” የሚለው “መሠረተ ቢስ” እንደሆነም ተናግሯል፡፡
ያልተረጋገጡ የግል መረጃዎችን የስደተኞች ናቸው በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማጋራቱ እንዲቆምም አሳስበዋል፡፡
ይህ በግለሰቦቹ፣ በቤተሰባቸውና በሱዳን በሚገኙ ስደተኞች ላይ ለበቀል እንደሚያነሳሳም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡