በዐቢዬ ግዛት የሚሰማራ ተተኪ ሰላም አስከባሪ ጦር ማፈላለግ መጀመሩን ተመድ አስታወቀ
ሱዳን በአቢዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በሌላ እንዲተካ መጠየቋ እና “ጥያቄዬ ተቀባይነት አገኘ” በሚል ማስታወቋ የሚታወስ ነው
ተመድ ዝርዝር መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሃገራት ወታደሮችን ማፈላለግ ጀምሬያለሁ ብሏል
በአቢዬ ግዛት የተሰማራውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ለመተካት መስፈርቱን የሚያሟሉ ሃገራትን ማፈላለግ መጀመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አስታወቀ፡፡
የተልዕኮው ረዳት ሚኒስትር ዣን ፒዬር ላክሮይክስ እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ፓርፋይት ኦናንጋ የተመራ ዓለም አቀፍ የልዑካን ቡድን ትናንት ማክሰኞ በካርቱም ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዱክ ተወያይቷል።
ውይይቱ በአቢዬ ግዛት ስለተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሱዳን ሰላም አስከባሪ ጦሩ በሌላ እንዲተካ መጠየቋ እና “ጥያቄያችን ተቀባይነት አገኘ” በሚል የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅ አል መህዲ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በውይይቱ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የልዑኩ መሪ ረዳት ሚኒስትር ዣን ፒዬር ላክሮይክስ ተቋማቸው አስፈላጊውን ዝርዝር መስፈርት የሚያሟሉ ሀገራት ወታደሮችን ማፈላለግ መጀመሩን አረጋግጠዋል።
የሰላም አስከባሪ ጦሩ መውጣት የሱዳንን መጠየቅ ብቻም ሳይሆን የደቡብ ሱዳንን መስማማትን የሚጠይቅም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦሯ የሚወጣ ከሆነ የሚወጣው “ተገቢውን ክብር አግኝቶ” እንደሆነ መግለጿ ይታወሳል፡፡
በተመድ የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ማዕቀፍ ስር ያለው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ጦር 13ኛ ሻለቃ ላበረከተው የነቃ ግዳጅ አወጣጥና ተልዕኮ አፈጻጸም እንዲሁም የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል መለስ ይግዛ ላሳዩት የላቀ አመራር ብቃት ከሰሞኑ የዕውቅና የምስክር ወረቀት እና ሜዳሊያ ሽልማት ማግኘታቸውን ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማስታወቁም የሚታወስ ነው፡፡