የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የትናንትናው ውሳኔ አንዲት ሉዓለዊት ሀገር ለመቅጣት ያለመ ህገ-ወጥ ውሳኔ ነው” ብሏል
ሩሲያ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔን ተከት ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነቷን አቋረጠች፡፡
ሩሲያ ከአባልነት የወጣችው በትናትናው እለት በተካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ከሰብአዊ መብቶች ም/ቤት መታገዷን ተከትሎ እንደሆነም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ " በኒውዮርክ የተላለፈው ሩሲያን የማገድ ውሳኔ ህገ-ወጥ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው እንዲሁም ገለልተኛ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲን የምትከትል አንዲት ሉዓላዊትና የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገር ለመቅጣት ያለመ ነው " ብለዋል፡፡
"በሰብአዊ መብቶች መስክ ማን እንደኛ የሚሉ መንግስታት ፤ራሳቸውን በጅምላ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ይገኛሉ" ያለው የሚኒሰቴሩ መግለጫ፤ ሩሲያ አሁንም ቢሆን ለሰብአዊ መብት ጥበቃ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቋል።
የትናንትናው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የተላለፈው ውሳኔን ተከትሎ ፤ በተመድ የሩሲያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ጋንዲ ኩዘሚን ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
የጉባዔውን ውሳኔ "ህጋዊ ያልሆነ፣ ፖለቲካው ዓላማ ያነገበ እንዲሁም የአንዲት ሉዓላዊት ሀገርን ስም ለማጠልሸት የታሰበ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል ጋንዲ ኩዘሚን፡፡
ምክር ቤቱ በጥቂቶች እጅ ወድቆ የነሱን ፍላጎት ማስፈጸምያ ሆነዋል ያሉት የሩሲያው ተወካይ፤ "እንዲህ ያሉት ተግባራት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ : ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የሰጠውን አደራ የሚጻረር እንዲሁም በዚህ አካል ላይ ያለውን እምነት የሚጎዳ ነው" ሲሉም አክሏል።
ኢትዮጵያ የተቃውሞ ድምጽ ያሰማችብትና በትናንትነው እለት የተሰለጠው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፤ ሩሲያን ከሰብአዊ መብቶች ም/ቤት አገዷል፡፡
193 አባላት ባሉት ጠቅላላ ጉባኤ፣በ93 ሀገራት ድጋፍ፣በ58 ድምጸ ተአቅቦ እና በ24 ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምጽ ሩሲያን ከሰብአዊ መብቶች ም/ቤት ለማገድ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ማጸደቁምን የሚታወስ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ እግዱን የጣለው ሩሲያ በዩክሬን ባካሄደችው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ወታደሮቿ መጠነ ሰፊ እና ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ግልጽ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን፤ ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በሪፖርት ገልጿል።
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24፣ 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
የዩክሬን ሃይሎች ጠንካራ ተቃውሟቸውን የፈጠሩ ሲሆን ምዕራባውያን ሩሲያ ኃይሏን እንድታስወጣ ከፍተኛ ማዕቀብ ጥለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ በቅረቡ ማጸደቁም አይዘነጋም።