የማይከበር ከሆነ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ነው ያስጠነቀቀው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በእስራኤል እና በእስላማዊ ጂሃድ ታጣቂዎች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሱን ተከትሎ አስቸኳይ ስበሰባ አደረገ፡፡
ስብሰባው በድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት የተደረገ ነው፡፡
የድርጅቱ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ተኩስ አቁም ቢደረግም እምብዛም አስተማማኝ አለመሆኑን በመጠቆም ሁለቱ አካላት ዳግም ወደ ግጭት የሚገቡ ከሆነ ጉዳቱ ሊከፋ ይችላል ሲሉ በስብሰባው ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች አጸፋዊ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ ሁኔታዎችን የበለጠ ሊያከፋ እንደሚችልም ነው ልዩ መልዕክተኛው የተናገሩት፡፡
መፍትሔዎችን ለመፈለግ የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያወሳስብ ይችላልም ብለዋል፡፡
እስራኤል ካሳለፍነው አርብ ጀምሮ በነበሩ ተከታታይ ሶስት ቀናት ዒላማ ባደረገቻቸው የታጣቂዎቹ ይዞታዎች ከባድ ድብደባዎችን ፈጽማለች፡፡ ታጣቂዎቹም በመልሱ 1100 ገደማ ሮኬቶችን አስወንጭፈዋል፡፡ በዚህም 15 ህጻናትን ጨምሮ 44 ሰዎች ሲገደሉ 360 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ሆኖም ከተተኳሾቹ 20 በመቶ ያህሉ በተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች መውደቃቸውን ነው ልዩ መልዕክተኛው ቶር ውንስላንድ በድንገት ለተሰበሰው ምክር ቤት የተናገሩት፡፡
እስራኤል ከየትኛውም አቅጣጫ የሚወነጨፉ ሮኬቶችንና ሌሎች ተተኳሾችን ለማምከን የሚያስችል አይረን ዱምን መሰል ዘመናዊ መሳሪያዎችን መታጠቋን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
የእስራኤልን የደህንነት ስጋት ያነሱት ልዩ መልዕክተኛው ታጣቂዎቹ ተመጣጣኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ሮኬቶችን ማስወንጨፋቸውን ኮንነዋል፡፡
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን ታጣቂዎቹ በንጹሃን መካከል በመሸሸግ ወደ ንጹህ እስራኤላውያን መተኮሳቸውን በማውገዝ ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም ቢሆኑ እስራኤል ዜጎቿን ከአሸባሪዎች ጥቃት የመጠበቅ መብት አላት ብለዋል፡፡
ሆኖም በድርጅቱ የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ መንሱር የእስራኤል ድርጊት ወረራ ነው በሚል ጥቃቱን ተቃውመዋል፡፡ ስንት ንጹሃን እስኪገደሉ ነው በሚልም ተመድ በቃ እንዲል ጠይቀዋል፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የዘለቀው ውጊያ በግብጽ አግባቢነት ለጊዜው እንዲቆም ስምምነት ላይ መደረሱ ይተቃወሳል፡፡