በሱዳን የእርዳታ እህል መዘረፉን የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ
የድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ፥ የሰብአዊ ድጋፎች ያለችግር የሚያልፉበት መስመር ሊከፈት ይገባል ብለዋል
በሱዳን ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ ማቆም ስምምነት ቢደረስም ውጊያው መቀጠሉ ተነግሯል
የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ የሚተላለፉባቸው ከውጊያ ነጻ መስመሮችን ክፍት እንዲያደርጉ የመንግስታቱ ድርጅት አሳስቧል።
የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ፥ በስድስት ተሽከርካሪዎች ላይ የተጫነ የእርዳታ እህል መዘረፉን ነው የተናገሩት።
ተፋላሚዎቹ ወገኖች የደህንነት ማረጋገጫ ቢሰጡንም ወደ ምዕራባዊ ዳርፉር እየተጓጓዘ የነበረው የሰብአዊ ድጋፍ መንገድ ላይ ቀርቷል ነው ያሉት።
ግሪፍትስ ከተዋጊ ጀነራሎቹ ጋር ትናንት በስልክ ሲወያዩም ይሄንኑ ጉዳይ በጥብቅ እንደተወያዩበት ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናት በካርቱም አልያም በሌላ ከተማ ከጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ዳጋሎ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ነጻ የሰብአዊ ድጋፍ ኮሪደር እንዲከፈት ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉም ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ትናንት በፖርት ሱዳን ቆይታ አድርገው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ጂዳ ያቀኑት የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ በካርቱም አልያም በሌሎች ከተሞች ከጀነራሎቹ ጋር ፊት ለፊት ለመምከር ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
46 ሚሊየን የሱዳን ህዝብ የሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ሶስተኛ ሳምንቱን የያዘው ጦርነት በዚሁ ከቀጠለም አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ እንደሚያስከት ነው ድርጅቱ ያሳሰበው።
ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናውያንን ለስደት የዳረገው ጦርነት እንዲበርድ ተፋላሚዎቹ ለሰባት ቀናት ተኩስ ለማቆም ተስማምተናል ቢሉም አሁንም የተኩስ ድምጹ አልበረደም ተብሏል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል መሪዎች በሰባት ቀናት ውስጥ ለድርድር የመረጧቸውን ሰዎች ስም ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት መግለጻቸው ይታወሳል።
የሱዳን ጦርም በኢጋድ የተመረጡት የኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ ፕሬዝዳንቶች በሚመሩት ንግግር ላይ የሚሳተፈውን ልኡክ እልካለሁ ብሏል።