ኤርትራ ግጭቱን ለሚሸሹ ሱዳናዊያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን በሬ ክፍት ነው ብላለች
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሀገራቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የሱዳን ግጭት አንገብጋቢ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል።
ሱዳን ነጻነቷን ካገኘችበት እ.አ.አ ከ1956 በኋላ ስለተጓዘችበት ሦስት የፖለቲካ ምዕራፎች ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ነባራዊ ሁኔታ ዐውደ ሰጥተዋል።
ሱዳን እስከ 1989 ድረስ የፖለቲካ ባህልና የእድገት መስመሯ በንጽጽር ከአህጉሩ የተሻለ ነበር ያሉት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ሆኖም በቀጣዮቹ ሦስት አስርት ዓመታት በብሄራዊ እስላማዊ ግንባር ፓርቲ ምክንያት መስመሯን ስታለች ብለዋል።
- ሱዳናዊው ጄነራል መሐመድ ዳጋሎ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በምን ጉዳይ መከሩ ?
- ኤርትራ ወደ ኢጋድ ልትመለስ መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስታወቁ
ካርቱም "መርዘኛ" ባሉት ፖሊሲ ምክንያት የአካባቢያዊ አለመረጋጋት ማዕከል ሆናለች ሲሉም በይነዋል።
በ2019 በሰራዊቱ የተደገፈው ድንገተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ በሰላሳ ዓመታት የግንባሩን የአስተዳደር ብልሹነት ለማስተካከል የመጣ ነው ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኤርትራ እንደሌሎች የቀጣናው ሀገራት፣ ከ2019 ጀምሮ ከሱዳን ፓርቲዎች በተለይም ከሉዓላዊው ም/ቤቱ ጋር የነቃ ተሳትፎ እና ምክክር ማድረጓን ተናግረዋል።
አስመራ በሱዳን የተፈጠረው አለመግባባት የሽግግሩን ሂደት እንዳይቀለብሰው መፈታት እንዳለበት ብላ ታምናለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አክለውም የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የለውጥ ሂደቱን በብቸኝነት የሙጥኝ የሚሉበት ጊዜ አይደለም።
"ይህ ጊዜ የፖለቲካ ንትርክ ወይም የስልጣን ሽኩቻ አይደለም" ብለዋል።
በሱዳን ውስጥ "አሃዳዊ" የመከላከያ እና የደህንነት ኃይል አስፈላጊነት ላይ ምንም አይነት ውዝግ ሊኖር አይችልም ሲሉም ኢሳያስ አፈወርቂ አክለዋል።
ነገር ግን ሲሉ እርጋታን የጠየቁት የኤርትራ ፕሬዝዳንት፤ ይህን እውነታ የፈጠረው የእስላማዊ ግንባር በመሆኑና ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውጭም ታጣቂዎች በርካታ በመሆናቸው፤ ጉዳዩ በስክነት መታየት አለበት ብለዋል።
የተዛቡ ያሏቸውን ድርጊቶች የማረም ስራው ለሱዳን ህዝብ የወደቀ ነው ብለዋል።
"የሱዳን ጎረቤቶች በተናጥል እና በኢጋድ በኩል የሱዳን ህዝብ የሚፈልገውን አዲስ የፖለቲካ ሂደት መፍጠር በሚያስችል ከባቢን ማመቻቸት ይችላሉ" በማለት ለችግሩ ቀጣናዊ መፍትሄ ጠቁመዋል።
ኤርትራ ድንበር በመክፈት ሱዳናዊያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን እንደምትቀበል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስታውቀዋል።