ደቡብ አፍሪካ አንድ ሚሊዬን የኮሮና ክትባቶች ዛሬ ትረከባለች
ቫይረሱን በፊትአውራሪነት እየተዋጉ ያሉ የጤና እና ሌሎችም ባለሙያዎች ‘ኮቪ ሺልድ’ ይሰኛል የተባለውን ክትባት ቀድመው ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ክትባቶቹ በህንድ ተመርተው በኤሚሬትስ አየር መንገድ ደቡብ አፍሪካ የሚደርሱ ናቸው
ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያዎቹን አንድ ሚሊዬን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ዛሬ እንደምትረከብ አስታወቀች፡፡
ክትባቶቹ በአስትራ ዜናካ ተዘጋጅተው ሴረም የተሰኘው የህንድ የመድሃኒት አምራች ተቋም ተመርተዋል፡፡ ከህንድ ፑን ከተማ የሚመጡም ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በኤሚሬትስ አየር መንገድ ተጭነው በመጓጓዝ ላይ ያሉትን ክትባቶች ኦሊቨር ታምቦ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው እንደሚቀበሉም የሃገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
ክትባቶቹ የመጡበት ጊዜ በብዙ ምክንያቶች ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ዝዌሊ ሚኬዚ ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱን በፊትአውራሪነት እየተዋጉ ያሉ የጤና እና ሌሎችም ባለሙያዎች ‘ኮቪ ሺልድ’ ይሰኛል የተባለውን ክትባት ቀድመው እንደሚያገኙም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ክትባቱ ከ62 በመቶ እስከ 90 በመቶ የማዳን ዐቅም እንዳለው ተነግሮለታል፡፡ ተከታቢዎቹ በአራት እና በስድስት ሳምንታት ልዩነት ሁለት ክትባቶች ሊያስፈልጓቸው እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ክትባቱን ለመጀመር የሚያስችላትን የኤሌክትሮኒክ የምዝገባ ሂደት ጀምራለች፡፡
67 በመቶ ወይም 40 ሚሊዬን ያህል ወጣቶችን ለመከተብም አቅዳለች፡፡ ይህ ደቡብ አፍሪካውያን ቫይረሱን ለመቋቋም የሚያስችል ጸረ እንግዳ አካል (አንቲቦዲ) በሰውነታቸው እንዲያዘጋጁ ለማድረግ (ኸርድ ኢሚዩኒቲ) የሚያስችል ነው፡፡
45 ሺ ገደማ ሰዎች በሞቱባት ደቡብ አፍሪካ 1 ነጥብ 4 ሚሊዬን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የሚታወስ ነው፡፡