የክትባት ስራውን የሚያስተባብር ግብረሃይል በብሄራዊ ደረጃ መቋቋሙንም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
የኮሮና መከላከያ ክትባት እስከ መጪው ሚያዝያ ወር ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባና 20 ከመቶ ለሚሆኑ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚዳረስ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የክትባት ስራውን የሚያስተባብር ግብረሃይል በብሄራዊ ደረጃ መቋቋሙንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የክትባትና ተያያዥ ጉዳዮች የሚኒስትሯ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሙሉቀን ዮሃንስ እንደገለፁት፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር እና ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት የኮሮና መከላከያ ክትባትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የእቅድና አጠቃላይ የዝግጅት ስራን በሚመለከትም የክትባቱን ሥራ የሚያስተባብር ግብረሃይል ከልማት አጋር ድርጅቶች፣ ከመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ በብሔራዊ ደረጃ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
ይህም ግብረ ሃይል የክትባት አቅርቦት አገልግሎቱን አጠቃላይ እቅድ እና ስራውን እየገመገመ የሚመራ፣ የማህበረሰብ ቅስቀሳ ትምህርትን የሚከታተል፣ ከክትባት ጋር በተያያዘ ያሉ አቅርቦቶችን የሚመራ፣ የክትባት ጥራትና ደህንነትን የሚቆጣጠር ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ከክትባት ጋር ተያይዞ የቅኝት፣ በሽታውን የመከላከልና የምርምርና ጥናት ስራ የሚያከናውን መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።