ተመድ፤ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ የተገደለችው በእስራኤል ወታደሮች ነው አለ
የእስራኤል ባለስልጣናት በግድያው ላይ ምርመራ አለማድረጉ አሳዛኝ ነው ተብሏል
ጋዜጠኛዋ የተገደለችው በፈረንጆቹ ግንቦት 11 ነበር
የ 51 ዓመቷ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አግላ የተገደለችው በእስራኤል ወታደሮች መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ።
በዘገባ ላይ ሳለች የተገደለችው የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ህይወቷ ያለፈው ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ነው ሲልም ነው ተመድ በግኝቱ ያነሳው። ጋዜጠኛዋ የዘገባ መታወቂያ (ፕሬስ) እና ሄልሜት አድርጋ ስትዘግብ እንደነበር ተገልጿል።
ፍልስጤማዊና አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አግላ የተገደለችው በፈረንጆቹ ግንቦት 11 ቀን 2022 ነበር።
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ በጄኔቫ እንደተናገሩት ጋዜጠኛዋን የገደሏት የእስራኤል ወታደሮች እንደሆኑ ገልጸዋል። ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ የእስራኤል ባለስልጣናት በጋዜጠኛዋ ግድያ ላይ ምርመራ አለማድረጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
በጥቃቱ ከተገደለችው ጋዜጠኛ በተጨማሪም ሌላ ጋዜጠኛ መጎዳቱን ያነሳው ተመድ ጥቃቱን ያደረሱት የፍልስጤም ተዋጊዎች ሳይሆኑ የእስራኤል ወታደሮች ናቸው ብሏል።
ጋዜጠኛዋ በእስራኤል ጦር መገደሏንም የምትሰራበት ተቋም አልጀዚራ ተናግሮ ነበር።
የጋዜጠኛዋ ግድያ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ጋዜጠኛዋ የተገደለችው በእስራኤል መከላከያ ኃይል እና በፍልስጤም መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድያው ወቅት ይህንን ቢሉም ጋዜጠኛዋ ተገደለችው በእስራኤል ጦር መሆኑ ግን በስፋት ሲወራ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጠኛዋ በአሳዛኝ ሁኔታ የተገደለች ቢሆንም የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን እስራኤልን ለመወንጀል ተጣድፈዋል ያሉ ሲሆን ጋዜጠኛዋ የተገደለችው በፍልስጤም የመሆን ዕድል እንዳለውም ገልጸዋል።