በዘገባ ላይ የነበረችው የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ተገደለች
ጋዜጠኛዋ በጄኒን ከተማ ስትዘግብ ነበር ተብሏል
እስራኤል ግድያው በተኩስ ልውውጥ የተፈጠረ ነው ብላለች
የ 51 ዓመቷ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አግላ በዘገባ ላይ ሳለች መገደሏን ደርጅቱ አስታወቀ፡፡
ጋዜጠኛዋ የተገደለችው የዘጋቢነት መለያዋን እንዳደረገች መሆኑም ተገልጿል፡፡ ጋዜጠኛዋ በእስራኤል ጦር መገደሏንም ተቋሟ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ጋዜጠኛዋ ከመገደሏ በፊት በጄኒን የስደተኞች ጣቢያ አካባቢ ስትዘግብ ነበር ተብሏል፡፡
የጋዜጠኛዋ ግድያ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ጋዜጠኛዋ የተገደለችው በእስራኤል መከላከያ ኃይል እና በፍልስጤም መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም ጋዜጠኛዋ ተገደለችው በእስራኤል ጦር መሆኑ ግን በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጠኛዋ በአሳዛኝ ሁኔታ የተገደለች ቢሆንም የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን እስራኤልን ለመወንጀል ተጣድፈዋል ያሉ ሲሆን ጋዜጠኛዋ የተገደለችው በፍልስጤም የመሆን ዕድል እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ህይወቷ ካላፈው ጋዜጠኛ በተጨማሪም ሌላ ፍልስጤማዊ ጋዜጠኛ መቁሰሉም ተገልጿል፡፡ አሊ አል ሳማውንድ የተባለውና እንደቆሰለ የተገለጸው ጋዜጠኛ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡