በአሜሪካ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያለው መንገድ በጋዜጠኛ ጀማል ጋሾጊ ስም ተሰየመ
ጋዜጠኛው ከቱርካዊት ፍቅረኛው ጋር ለመጋባት በሂደት ላይ እያለ ነበር የተገደለው
ጋዜጠኛ ጀማል ጋሾጊ በሳዑዲ ባለስልጣናት ትዕዛዝ በቱርክ አንካራ መገደሉ ይታወሳል
በአሜሪካ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያለው መንገድ በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ስም ተሰየመ፡፡
ለዋሸንግተን ፖስት ተነባቢ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ከሁለት ዓመት በፊት ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ቀጥተኛ ትዕዛዝ መገደሉ የተገለጸው ጋዜጠኛ ጀማል በሳዑዲ ንጉሳዊ መንግስት ላይ በሚሰነዝራቸው ተደጋጋሚ ትችቶች ምክንያት ሊገደል መቻሉን በወቅቱ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይፋ መደረጉም አይዘነጋም፡፡
የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛው ከቱርካዊት ፍቅረኛው ጋር በኢስታንቡል ጋብቻ ለመፈጸም አስፈላጊ ሰነዶችን ከሳዑዲ ኢምባሲ ለማውጣት በገባበት ወቅት ነው በደህንነቶች ተይዞ ተገደለ የተባለው፡፡
ድርጊቱ በወቅቱ በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን በተለያዩ ሀገራት ያሉ ዜጎች በሳውዲ ኤምባሲዎች በመቅረብ ተቃውሟቸውን ከማሰማታቸው ባለፈ ቱርክ ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል በሚል ከፍተኛ ቅሬታን አቅርባም ነበር፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት መቀዛቀዝ ያሳየ ሲሆን አሁን ላይ መሻሻል እየታየበት መሆኑ ይገለጻል፡፡
ዋሸንግተን ከሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያለው መንገድ “ጀማል ካሾጊ ጎዳና” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የመታሰቢያ መንገዱን የሳዑዲ እና አሜሪካ ዲፕሎማቶች በተገኙበት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሙያተኞች በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ በሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ቀጥተኛ ትዕዛዝ እንደተገደለ ሲአይኤ ሪፖርት ቢያቀርብም አልጋ ወራሹ ሪፖርቱን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ ከሳምንት በኋና ወደ አንካራ ለይፋዊ ጉብኝት እንደሚጓዙ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በያዝነው ሰኔ ወር ላይ ሪያድን የመጎብኘት እቅድ ቢያዙም እስካሁን ይፋ ባልሆነ ምክንያት ጉብኝታቸውን ለአንድ ወር አራዝመዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎም በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው የሳዑዲ እና አሜሪካ ግንኙነት ሊሻሻል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡