የስርዓተ-ጾታ አድሎአዊነት ባለፉት አስር ዓመታት አልተሻሻለም- ተመድ
የባህል አድልዎ እና ጫናዎች በ2030 የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ አደናቀፈ
ከዓለም ህዝብ ግማሽ ያህሉ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የተሻሉ የፖለቲካ መሪዎች ናቸው ብለው ያምናሉ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስርዓተ-ጾታ ኢ-እኩልነት ለአስር ዓመታት ቆሞ እንደቆየ ይፋ ባደረገው ጥናት ገልጿል።
የባህል አድልዎ እና ጫናዎች የሴቶችን አቅም ማደናቀፉን መቀጠሉ የተናገረ ሲሆን፤ ይህም በመሆኑ በ2030 የተያዘው የጾታ እኩልነት ግብ እንዳይሳካ አድርጓል ብሏል።
በአሜሪካ ውስጥ እንደ ታይም አፕ እና ሚ ቱ ያሉ ማህበራዊ ንቅናቄዎች ብቅ ቢሉም፤ አድሏዊ የሆኑ ማህበራዊ ደንቦች እና በኮቪድ-19 የተባባሰው የሰው ልማት ቀውስ በጾታ እኩልነት ላይ መሻሻል እንዳይታይ አድርጓል ተብሏል።
85 በመቶ የዓለምን ህዝብ በሚሸፍኑ ሀገራት እና ግዛቶች ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2014 እና ከ2017 እስከ 2022 በተደረገ ጥናት ከ10 ሰዎች ዘጠኙ በሴቶች ላይ መሰረታዊ የሆነ አድሏዊነት አላቸው።
በጥናቱ ከተካተቱት 38 ሀገራት ቢያንስ አንድ አድልዎ ያላቸው ሰዎች ድርሻ ከ86.9 በመቶ ወደ 84.6 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የተመድ የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የምርምር እና ስልታዊ አጋርነት አማካሪ እና የሪፖርቱ ተባባሪ የሆኑት ሄሪቤርቶ ታፒያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ያለው መሻሻል ተስፋ አስቆራጭ ነው ብለዋል።
ከዓለም ህዝብ ግማሽ ያህሉ ወንዶች የተሻሉ የፖለቲካ መሪዎች ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።
43 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ወንዶች የተሻሉ ስራ አስፈጻሚዎች ናቸው ብለው እንደሚያስቡ ጥናቱ አመልክቷል።