ኢትዮጵያዊቷ መዓዛን ጨምሮ 11 ሴቶች “የዓለም አቀፍ የጀግና ሴቶች ሽልማት” አሸናፊ ሆኑ
ከ2007 ጀምሮ ከ80 ሀገራት የተገኙ ከ180 በላይ ጀግና ሴቶች እውቅና አግኝተዋል
ተሸላሚዎቹ ከባድ ፈተናዎችን አልፈው ለሰው ልጆች የሚጠቅም ስራ የሰሩ ጀግና ሴቶች ናቸው ተብሏል
ኢትዮጵያዊቷ መዓዛ መሐመድን ጨምሮ 11 ሴቶች በአሜሪካ መንግስት የተሰጠውን የ2023 “የዓለም አቀፍ የጀግና ሴቶች ሽልማት” አሸናፊ ሆነዋል።
ከተጀመረ 17ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የአሜሪካ “ዓለም አቀፍ የጀግና ሴቶች ሽልማት” በመላው ዓለም ከባድ አደጋዎችንና ፈተናዎችን ተቋቁመው ሰላም፣ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ የጾታ እኩልነት እና የሴቶች ተጠቃሚነት እንዲከበሩና እንዲሰፍኑ ልዩ ጥንካሬ፣ ጀግንነትና የአመራር ጥበብ ላሳዩ ሴቶች የሚበረከት ሽልማት ነው፡፡
- ኢትዮጵያ በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ የሴቶች ቁጥር ካላቸው የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ነች- ተመድ
- ታሊባን የአፍጋኒስታን ሴቶች ፊታቸውን እንደገና እንዲሸፍኑ መመሪያ ሰጠ
ለሽልማቱ የሚመረጡት ሴቶች የሚታጩት በየሀገራቱ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ሲሆን፤ የመጨረሻዋቹን አሸናፊዎች የሚመርጠው ደግሞ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡
ሽልማቱ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የሚዘጋጅ ሲሆን ከ2007 ጀምሮ ከ80 ሀገራት ለተገኙ ከ180 በላይ ጀግና ሴቶችን እውቅና ሰጥቷል፡፡
በዚሁ አመትም የሚኒስቴሩ ባለስልጣናት መስፈርቱን አሟልተዋል ያሏቸው 11 ጀግና ሴቶች ሸልሟል፡፡
ከተሸለሙት መካከል ኢትዮጵያዊቷ መምህርት፣ ጋዜጠኛና የስብአዊ መብቶች ተሟጋች መዓዛ መሐመድ አንዷ ናት፡፡
የ2023 “የዓለም አቀፍ የጀግና ሴቶች ሽልማት” አሸናፊዎች
1. መዓዛ መሐመድ - ኢትዮጵያ
2. ሐዲል አብደልአዚዝ - ዮርዳኖስ
3. ዶ/ር ዘካሪያ ሒክመት - በቱርክ የሚኖሩ
4. ዩሊያ ፓይቪስካ - ዩክሬን
5. ዳተክ ራስ አዲባ ራዲ - ማሌዢያ
6. ፕ/ር ዳንኤላ ዳርላን - መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ
7. አልባ ረውዳ -አርጀንቲና
8. ብ/ጀኔራል ቦሎር ጋንቦልድ - ሞንጎሊያ
9. ባክዛን ቶሬጎዚና - ካዛኪስታን
10. ቢያንካ ዛሌውስካ - ፖላንድ
11. ዶሪስ ሪዮስ - ኮስታ ሪካ ናቸው፡፡
ተሸላሚዎቹ በቀጣይ ቀናት በአሜሪካ ከተሞች ከሚገኙ አሜሪካውያን አቻዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እና የሴት መሪዎችን ዓለም አቀፋዊ ትስስርን ለማጠናከር በተዘጋጀው የዓለም አቀፍ የጎብኚዎች አመራር መርሃ ግብር (IVLP) የሚሳተፉ ይሆናል፡፡