በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ከ20 ሺ በላይ ስደተኞች ከሰፈሩበት ካምፕ መፈናቀላቸውን ተመድ ገለጸ
ተመድ ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ በቤኒሻንጉል ያለውን ሁኔታ “በጣም አስጨናቂ” ነውም ብለዋል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ70 ሺ የውጭ ስደተኞች እና ከ500ሺ በላይ የውስጥ ተፈናቃዮች ያስተናግዳል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ከ20 ሺ በላይ ስደተኞች ከሰፈሩበት ካምፕ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ገለጸ፡፡
ግጭቱ የተፈጠረው ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እና በፌደራል ሃይሎች መካከል እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታውቋል።
“ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ20 ሺ የሚበልጡ ስደተኞች ለክልሉ መዲና አሶሳ ከተማ አዋሳኝ በሆኑ አከባቢዎች ተበታትነው እርዳታ በመጠባበቅ ላይ ናቸው”ም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
በጥር 18 በቶጎ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በአቅራቢያው የሚገኝና 10 ሺ300 ስደተኞችን የሚያስተናግደው መጠለያ ጣቢያ መቃጠሉን እና መዘረፉንም የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ፡ ከዚህ ቀደም በታህሳስ ወር መጨረሻ በአካባቢው ሌላ መጠለያ ጣቢያ መዘረፉንም አስታውሷል።
በሁለቱ ቶንጎ እና ጉሬ-ሼምቦላን የተባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን “የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ከቀያቸው መፈናቀላቸው አሁን ላይ በሁለቱም መጠለያ ጣቢያዎች ለነበሩና በየአከባቢው ለተሰደዱ 22 ሺ ስደተኞች አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አለማቻሉ ጉዳዩ አሳሳቢ አድርጎታል”ም ብለዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ ያለውን ሁኔታ “በጣም አስጨናቂ” ነው ሲልያለው ኮሚሽኑ፤ ያለውን እግር ለመፍታትና እርዳታ ለማዳረስ ከኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት (RRS) እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለስልጣናት ለስደተኞች አጋርነታቸውን በማሳየታቸው እና 20 ሺ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል አዲስ ጊዜያዊ ቦታ ለይተው ስደተኞች እንዲጠለሉ ማድረጋቸው የሚመሰገን ነውም ነው ያለው ኮሚሽኑ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ70 ሺበላይ ሱዳናውያን እና ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች እንዲሁም ከ500ሺ በላይ ተፈናቃይ ኢትዮጵያውያንን ያስተናግዳል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ሌሎች ሶስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች (ባምባሲ፣ ሸርቆሌ እና ጾሬ) ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እንደሆኑ እና አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡