ቦርዱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሊያደርግ የነበረውን ምርጫ አቋረጠ
በቢኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታህሳስ ወር ምርጫውን ለማከናወን የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ተግባራትን ማከናወን ጀምሮ ነበር
ቦርዱ የምርጫ ዝግጅቱን ያቋረጠው በመላ ሀገሪቱ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑን አስታውቋል
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ሰሌዳን እና ዝግጅትን ያቋረጠ መሆኑን አስታወቀ።
ቦርዱ በዛሬው እለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫው፤ በቢኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታህሳስ ወር ምርጫ ለማከናወን የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ተግባራትን ማከናወን ጀምሮ እንደነበር አስታውቋል።
ሆኖም ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀውን አገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትናንትና ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ማጽደቁን ተቀትሎ የምርጫውን ሰሌዳን እና ዝግጅት ማቋጡን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫን በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች አከናውኖ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በቢኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄዱባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበረ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሔደው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በሀገር ህልውና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ያወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ የሚታወስ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም በትናትናው እለት ተቀብሎ አጽደቋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ አዋጁ የታወጀው በሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ ነው ማለታቸው ይታወሳል።