የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያጋጠሙት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከክልሉ ህገ-መንግሥት አግላይነት ጋር የተያያዙ ናቸው መባሉን ተቃወመ
ህገ-መንግሥቱ የሚፈርሰው የፌዴራል ስርዓቱ እንዲፈርስ ቅዥት የሚመኙ አካላት ሲሳካላቸው ብቻ ነው ሲል ዛሬ መግለጫ አውጥቷል
ክልሉ በአማራ ክልል ባለስልጣናት የሚዲያ ዘመቻ እየተደረገበት እንደሚገኝም አስታውቋል
በክልሉ ተደጋግመው ካገጠሙ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ባለስልጣናት የሚዲያ ዘመቻ እየተደረገብኝ ነው ሲል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ፡፡
ዘመቻዎቹ በየትኛውም መስፈርትና መመዘኛ ተቀባይነትና አግባብነት የላቸውም ያለው ክልሉ የፀጥታ ችግሮቹ ከክልሉ ህገ-መንግሥት አግላይነት ጋር የተያያዙ ናቸው መባሉንም ተቃውሟል፡፡
“የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ-መንግሥት የሚፈርሰው የፌዴራል ስርዓቱ እንዲፈርስ ቅዥት የሚመኙ አካላት ሲሳካላቸው ብቻ ነው” ሲልም ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የክልሉ ህዝቦች ባለፉት 27 ዓመታት በተጨባጭ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡን የሚያትተው መግለጫው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ያጋጠሙት የፀጥታ ችግሮች “ለውጡ ባልቸመቻቸው ጥቂት ቡድኖችና የግል የፓለቲካ ፍላጎት ባላቸው ፀረ-ሠላም ተልዕኮ ባነገቡ አካላት የሚፈጠሩ” ናቸው ብሏል፡፡
ይሁንና የአጎራባች የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከግጭቶቹ ጋር በተያያዘ የመንግስት ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር የክልሉን ነባራዊ እውነታና ተጨባጭ ሃቁን ባላገናዘበ መልኩ ችግሮቹ ከክልሉ ህገ-መንግሥት አግላይነትና በክልሉ ከሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በተመጣጣኝ አለመወከል ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ናቸው በማለት በሚዲያ ሲያስተጋቡ እንደሚስተዋልም ገልጿል፡፡
የክልሉን ህገ-መንግሥት የማሻሻል ስልጣን ክልሉን የመሰረቱት የ5ቱ ነባር ብሄረሰቦች ማለትም የበርታ፣ የጉሙዝ፣ የሽናሻ፣ የማኦና ኮሞ እና በክልሉ ለዘመናት አብረው የሚኖሩ ህዝቦች እንጂ ጥቂት የፓለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳልሆነ ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋልም ነው ያለው።
“የተዛቡ እና ፈጽሞ ሊሆኑ የማይችሉ” ያላቸው ‘መተከል የኛ ነው’ን ዓይነት ትርክቶች በአንዳንድ ግለሰቦችና የፓለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ሲስተጋቡ እንደሚውሉም ነው የገለጸው፡፡
“‘መተከል የኛ ነው’የሚለው የተዛባ ትርክት ምንዓልባትም እውን የሚሆንላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮችን፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ፈቅደውና አምነው ያጸደቁት የጋራ ቃል-ኪዳን የሆነው የፌዴራላዊ ስርዓትና ህገ-መንግሥቱ ሲፈርስላቸው ብቻ መሆኑን በውል ሊገነዘቡት ይገባል” ሲልም ነው ያስቀመጠው፡፡
የክልሉ መንግሥት በዞኑ አንዳንድ አከባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉንና የፌደራል የፀጥታ አካላትን በማስተባበርና በማቀናጀት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ይህ ባለበት ሁኔታ “በአማራ ክልል መንግስት በተለይም በከፍተኛ አመራሩ በኩል በየጊዜው በሚዲያ የሚደረገው ዘመቻና የጦርነት ነጋሪት መጎሰም በየትኛውም መስፈርትና መመዘኛ ተቀባይነትና አግባብነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ” እንደሚያስፈልግም አስታውቋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በመተከል ዞን በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ጥቃቱ ዘርን መሰረት አድርጎ የሚፈጸም ነው ያለው የአማራ ክልል መንግስትም ከአሁን በኋላ የሚፈጸሙ መሰል ጥቃቶችን እንደማይታገስ ገልጾ በክልሉ ያሉ የብሄሩ ተወላጆች ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ እና በክልሉ መንግስት የጸጥታ መዋቅር ጭምር እንዲካተቱ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቆ ነበር፡፡
የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫም የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ማስታጠቅን ጨምሮ በቅንጅት እንደሚሰሩ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡