በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንፁኃን ግድያ ከዚህ በኋላ ከቀጠለ እርምጃ እንደሚወስድ የአማራ ክልል አስታወቀ
የንፁኃንን ህይወት በግፍ መግደል ሊያበቃ እንደሚገባም ክልሉ አሳስቧል
በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን የአማራ ክልል ገልጿል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንፁኃን ግድያ ከዚህ በኋላ ከቀጠለ እርምጃ እንደሚወስድ የአማራ ክልል አስታወቀ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚደርሰውን የንፁኃን ዜጎች ግድያ ከዚህ በላይ በትዕግስት እንደማይመለከተው የአማራ ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡ ዜጎች በግፍ የሚገደሉበት ጊዜ ማብቃት እንዳለበትም ክልሉ አሳስቧል፡፡
በመተከል ዞን የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ "በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅሟል" ማለታቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
በክልሉ የሚስተዋለውን ጥቃት ለማስቆም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ እንደተሠራ የተናገሩት አቶ ግዛቸው የክልሉ መንግሥት ለተጎዱ ዜጎች ቦታው ድረስ በመሄድ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው ችግር መቀጠሉን ነው የገለጹት፡፡
በመተከል ዞን በዳንጉር፣ ጉባ፣ ማንዱራ፣ ወንበራና ቡለን ወረዳዎች በታቀደና በተደራጀ የታጠቀ ኃይል "ወገኖቻችን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል" ብለዋል፡፡
ጥቃት አድራሾቹ ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱት ብሔርን ከብሔር ጋር ማጋጨት እንደሆነና ቀጣናውን በተለይም አማራ ክልልን ማተራመስ መሆኑንም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይቶች ተደርገው "አቅጣጫ ቢቀመጥም እስካሁን ድረስ መሬት ላይ አልወረዱም" ያሉት አቶ ግዛቸው "የቤንሻንጉል ክልል መንግሥት መዋቅር ንጹሕ አለመሆን እና ዜጎችን ያገለለ ሥራ መሥራቱ ለችግሩ ምክንያት ነው" ብለዋል፡፡ "የማዕከላዊ መንግሥቱም ቢሆን ያደረገው ጥረት ጥሩ ቢሆንም ዜጎችን ግን ከሞት እያዳነ አይደለም" ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል መንግሥትም ቢሆን ችግሮችን በውይይትና በዴሞክራሲ ለመፍታት ብዙ የተደከመ ቢሆንም ነዋሪዎችን "ከጥቃት መታደግ አልተቻለም" ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም በቀጣይነት ሁለት ምርጫዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ አንደኛው የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጉዳዩን "በዋዛ ፈዛዛ ሳይመለከተው" የአማራ ክልል ተወላጆችን እንደሌላው የክልሉ ነዋሪ በሰላም እንዲኖሩ የማደራጀት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚያስችል ሥራ መስራት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
ሁለተኛው አማራጭ ግን "የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል እርምጃ እስኪወስድ ብቻ አንጠብቅም ብዙ ታግሰናል፤ እንደ አማራ ክልል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን አሠራሩ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግና ከቤኔሻንጉል ክልል መንግሥት ጋር በጥምረት በመሥራት የክልሉ ተወላጆች ከዚህ በኋላ ከጥፋት የመታደግ ሁኔታ የግድ ነው" ብለዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብም ከስሜታዊነት በመውጣት መንግሥትን መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የራሱን ሥራ ለመሥራት አቋም የወሰደ ስለሆነ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ እንዲደግፈውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡