የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን “በአዲስ አበባ ለሚገኙ 3ሺ990 ኤርትራውያን ስደተኞች” የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ
በማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣብያዎች ለሚገኙ 24ሺ 327 ስደተኞች ድጋፍ ማድረጉንም የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል
ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ዳባቱ “አለምዋጭ መጠለያ ጣብያ” የማዛወር ሂደት እየተከናወነ መሆኑም ገልጸዋል
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ /ዩኤን ኤች ሲ አር/ በአዲስ አበባ ለሚገኙ 3ሺ 990 ኤርትራውያን ስደተኞች” የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡
በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከወደሙት “የህፃፅና ሽመልባ መጠለያ ጣብያዎች” የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማምራታቸው ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች “አዲስ አበባ የሚገኙና የሶስት-ዓመት ሰነዶች ያሟሉ ኤርትራውያን ስደተኞች” ከተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸው ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡
በፈረንጆቹ ከነሃሴ 04 እስከ 19/2021 ባሉት ቀናት ብቻ 3ሺ 990 ወይም 3ሺ061 አባወራዎች ተመዝግበው የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነውም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡በቀጣይ 9ሺ የሚሆኑ ስደተኞች ለመርዳት ታቅዷል ብለዋል፡፡
ክሬቨንኮቪች በተቀሩት ሁለት የማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣብያዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድጋፍ እተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
“የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኤጀንሲ ከነሃሴ 5፤2021 ወዲህ ባሉ ጊዝያት በማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣብያዎች ለሚገኙ 8ሺ 739 አባወራዎች (24ሺ 327 ስደተኞች) ድጋፍ አድርጓል”ም ብለዋል ክሬቨንኮቪች ቃል አቀባዩ ኔቨን ክሬቨንኮቪች፡፡
በመጠልያ ጣብያዎቹ የሚገኙትን ኤርትራውያን ደህንነት ለመጠበቅ ስደተኞችን ወደ ሌላ ጣብያ የማዛወር ሂደት እየተከናወነ መሆኑንም አስታወቋል፡፡
የስደተኞች ኤጀንሲ በፈረንጆቹ ሃምሌ 29፡ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች ለ30 ቀናት ያክል በመጠልያ ጣብያዎች አከባቢ የሚያደርጉትን ተኩስ እንዲያቆሙ በጠየቀው መሰረት “በማይ ፀብሪ በሚገኙ ሁለቱ የማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣብያዎች” የነበሩ ስደተኞች ስደተኞችና ከስደት ተመለሾች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ወደ “ዳባት” ማዛወር ተጀምሯልም ነውም ብሏል፡፡
የስደተኞች ኤጀንሲው በዳባት አከባቢ “አለምዋጭ” በተበላ ስፍራ አዲስ መጠለያ ጣብያ ገንብቶ ለኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመለሾች ኤጀንሲ ማስረከቡን የገለጹት ቃል አቀባዩ “በጣብያው 25 ሺህ ስደተኞች የማስተናገድ እቅድ ተይዟል”ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምታት ብቻ 127 ስደተኞች ወደ ዳባት ተዛውረው፤ መጠለያን ጨምሮ አስፈላጊ የምግብና የቁሳቁስ እርዳታዎች እያገኙ ናቸው ሲሉም አክለዋል ቃል አቀባዩ፡፡ከፍተኛ የጤና ችግር ያለባቸው ስደተኞች ወደ ሌሎች ክልሎች ተዛውረው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነውም ብሏል፡፡
10 ወራት ገደማ ያስቆጠረው የትግራይ ግጭት አሁን ላይ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ ከፍተኛ የሆነ ስበዓዊ ቀውስ ማስከተሉ እጅጉን እንደሚያስጨንቀው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዝያት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎችና ስደተኞች አስፈላጊውን እርዳታ ለማዳረስ ሲሰራ መቆየቱና የግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህጎች እንዲያከብሩም እንዲሁ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡