ፖለቲካ
ኤርትራ፤ አሜሪካ በጦር መሪዋ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ "መሠረተ ቢስ" ስትል ውድቅ አደረገች
ኤርትራ "ህገ ወጥ" ያለችውን የአሜሪካን የማዕቀብ እርምጃ በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል መግለጫ አውጥታለች
ኤርትራ ውንጀላ እና ክሱን በደብዳቤም ሆነ በመንፈስ እንደማትቀበልም አስታውቃለች
ኤርትራ፤ አሜሪካ በጦር መሪዋ ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ (ፍሊጶስ) ላይ የጣለችውን ማዕቀብ "መሠረተ ቢስ" ስትል ውድቅ አደረገች።
ኤርትራ "ህገ ወጥ" ያለችውን የአሜሪካን የማዕቀብ እርምጃ በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል መግለጫ አውጥታለች።
የአሜሪካ አስተዳደር በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ (ፍሊጶስ) ላይ "ተቀባይነት የሌላቸውን ክሶች ሰንዝሯል" ያለው መግለጫው የኤርትራ መንግስት የተቃጣበትን መሠረተ ቢስ ውንጀላ እና ክስ በደብዳቤም ሆነ በመንፈስ እንደማይቀበል አስታውቋል።
የአሜሪካ አስተዳደር እንዲህ ዐይነት መሠረተ ቢስ የውንጀላ ዘመቻዎችን በኤርትራ ላይ ሲያርግ የመጀመሪያው እንዳይደለም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው የጠቆመው።
ባሳለፍነው ወርሃ መጋቢት መባቻ ላይ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳሌህ ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን "እንዳለመታደል ሆኖ በሚዲያዎች በሚነዙ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ላይ ተመስርተው ማደማደሚያዎችን ይሰጣሉ" ሲሉ በጻፉት ደብዳቤ "ተከታታይ የአሜሪካ አስተዳደሮች ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በኤርትራ ላይ ሲያራምዱት ወደነበረው ፖሊሲ የተመለሱ በሚያስመስለው ደብዳቤዎ አዝኛለሁ" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው እንደነበር አስታውሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች አልገባም ባሉበት በዚህ ደብዳቤ መፍትሔዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ስለመግለጻቸውም ነው በመግለጫው የተጠቀሰው።
ኤርትራ ምክንያታዊ ያልሆኑ ተደጋጋሚ ክሶችን በዝምታ ልታልፍ እንደማትችልም ይጠቁማል።
"ሃሰተኛ" ያለው ውንጀላ ሊጣራ የሚችል ነገር ካለው በገለልተኛ አካል እንዲጣራም ለአሜሪካ አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ የዓለም አቀፍ ህግጋትና የሃገራትን የሉዓላዊነት ጥሰቶች በመግታት እና መፈትሔ በመፈለግ ረገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስቧል።
በትግራይ ጦርነት የሚመሩት ጦር የተለያዩ ሰብዓዊ ጥሰቶችንና ግድያዎችን ፈጽሟል ያለው የአሜሪካ ፌዴራል ግምጃ ቤት (ትሬዠሪ) ጄነራል ፊሊጶስ በአሜሪካ አላቸው ያለውን ሃብት እንዳያንቀሳቅሱ ማገዱን ዛሬ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።