ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ለትግራይ ክልል የ500 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረጉ
“ረሃብን ለመከላከል፣ ንፁሃን ዜጎችን ለመጠበቅና ህይወት ለማዳን በጋራ መንቀሳቀስ አለብን”- የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች
መንግስት የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በሰጠው መግለጫ ላይ አሜሪካ ተሳትፋለች
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ለትግራይ ክልል የሚውል የ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸው ተነግሯል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶቹ በጋራ በመሆን ድጋፉን ማድጋቸውን የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ቢሮ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
ህብረቱ ባወጣው መረጃ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶቹ የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረገ ያለውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
“ረሃብን ለመከላከል፣ ዜጎችን ለመጠበቅ እና ህይወት ለማዳን በጋራ መንቀሳቀስ አለብን” ብለዋል የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶቹ።
ሁሉም ተዋጊ ሀይሎች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያደርሱ አካላት መንገድ እንዲከፍቱም ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲም በትዊተር ገጹ ባወጣው መረጃ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች የሰጠው መግለጫ ላይ አሜሪካ መሳተፏን አስታውቋል።
ሁሉም ተዋጊ ሀይሎች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ የጠየቀው ኤምባሲው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅትቶች እና ጋዜጠኞች ያለገደብ በክልሉ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ መደረግ እንደሚገባውም ጠቁሟል።