የራፋ ወረራ ከፍተኛ "ደም መፋሰስ" ያስከትላል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ
የመጨረሻዎቹ የሀማስ ምሽጎች በራፋ እንደሚገኙ የገለጸችው እስራኤል ሀማስን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ የሚቻለው ራፋን ስትቆጣጠር መሆኑን ገልጻለች
የደቡብ አፍሪካ መንግስት አለምአቀፉ ፍርድ ቤት የእስራኤልን የራፋ ጥቃት እቅድ አስቸኳይ እርምጃዎች ያስፈልጉት እንደሆነ እንዲመረምረው ጥያቄ አቅርቧል
የራፋ ወረራ ከፍተኛ "ደም መፋሰስ" ያስከትላል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ።
እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠልሎባት የምትገኘውን የጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋን በእግረኛ ጦር የምታጠቃ ከሆነ "ከፍተኛ ደም መፋሰስ" ሊከሰት ይችላል ሲል ተመድ አስጠንቅቋል።
የመጨረሻዎቹ የሀማስ ምሽጎች በራፋ ይገኛሉ ያለችው እስራኤል ሀማስን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ የሚቻለው ራፋን ስትቆጣጠር መሆኑን ገልጻለች።
"በራፋ የሚደረግ ወታደራዊ ጥቃት ወደ ደም መፋሰስ ያመራል። በከፍተኛ ደረጃ የተባባሰውን የጋዛ የሰብአዊ ቀውስ ወደ ከፋ ደረጃ ያሸጋግረዋል" ሲሉ የተመድ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ተናግረዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ "በጋዛ የሚደረግ ወረራ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል አለምአቀፉ ማህበረሰብ እያስጠነቀቀ ነው፤ የእስራኤል መንግስት ይህን ችላ ማለች አይችልም" ብለዋል።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የእስራኤል የራፋ ወረራ ለማስቀረት ታጋቾችን የመልቀቅ እና ግጭት የማቆም ስምምነት ይደረሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
እስራኤል ራፋን የምትወር ከሆነ አደጋው የከፋ ይሆናል ብለዋል ጉተሬዝ።
በተመሳሳይ እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል የከሰሰው የደቡብ አፍሪካ መንግስት አለምአቀፉ ፍርድ ቤት የእስራኤልን የራፋ ጥቃት እቅድ አስቸኳይ እርምጃዎች ያስፈልጉት እንደሆነ እንዲመረምረው ጥያቄ አቅርቧል።
ደቡብ አፍሪካ በእሰራኤል ላይ ያቀረበችውን ክስ የተመለከተው አለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) እስራኤል ጦሯ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይፈጽም እንድታደርግ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
እስራኤል ግን የቀረበባትን የዘር ማጥፋት ክስ አልተቀበለችውም።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ የደቡብ አፍሪካ መንግስት እስራኤል በራፋ አደርገዋለሁ ያለችው ወታደራዊ ጥቃት የከፍ ግድያ እና ውድመት የሚያስከትል በመሆኑ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ለፍርድ ቤቱ ባስገባው ጥያቄ ጠቅሷል።
"ይህ የዘር ማጥፋት ህግን እና ፍርድ ቤቱ ጥር 26 ያስተላለፈውን ውስኔ የሚጥስ ነው"
መቀመጫው ሄግ ያደረገው ፍርድ ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ደቡብ አፍሪካ ያቀረበችውን ጥያቄ መቀበሉን አረጋግጧል። ነገርግን ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ መቼ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አልገለጸም።
ከዚህ በፊት በነበሩ አሰራሮች ፍርድ ቤቱ መሬት ያሉ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ተጨማሪ አስቸኳይ እርምጃዎችኝ የሚወስድበት አሰራር አለው።
የእስራኤን ራፋን የማጥቃት እቅድ የግጭቱ አደራዳሪዎች እና ግብጽ ተቃውመውታል።
በተለይም ግብጽ እስራኤል በራፋ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ ከእስራኤል ጋር ከ40 አመታት በፊት በካምፕ ዴቪድ የፈረመችውን የሰላም ስምምነት ልትሰርዘው እንደምትችል አስፈራርታለች።