እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘውን ራፋን ለማጥቃት ትኩረት ማድረጓ ተገለጸ
እስራኤል ራፋን ለማጥቃት እየተንቀሳቀሰች ያለችው ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚወተውቱ ጫናዎች በመጨመሩበት ወቅት ነው
በጦርነቱ ምክንያት 2.3 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚኖሩት በራፋ ነው ተብሏል
እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘውን ራፋ ለማጥቃት ትኩረት አድርጋለች ተብሏል።
በደቡባዊ የጋዛ ከተማ ካን ዩኒስ ሀማስን መደምሰሷን የገለጸችው እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘውን ራፋ ለማጥቃት እየተዘጋጀች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል ራፋን ለማጥቃት እየተንቀሳቀሰች ያለችው ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚወተውቱ ጫናዎች በመጨመሩበት ወቅት ነው።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዩአቭ ጋላንት እስራኤል በካን ዩኒስ የፍልስጤሙን ታጣቂ መደምሰሷን እና ይህም ማለት የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛዋ የድንበር ከተማ ራፋ ያቀናል ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት 2.3 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚኖሩት በራፋ ነው ተብሏል።
ጋላንት "በካን ዩዮኒስ ያቀድነውን ግብ አሳክተናል። ወደ ራፋ በማምራት ችግር የሚያሰጉንን የሽብር አካላትን እናጠፋለን" ብለዋል።
በዚህ ወቅት ግብጽ እና ኳታር ሀማስ ባለፈው ሳምንት በፖሪስ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ጦርነቱን ረዘም ላለጊዜ ለማቆም የተደረሰውን ስምምነት ይቀበለዋል በሚል ተስፋ እየጠበቁ ናቸው።
ሮይተርስ የፍልስጤም ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ጦርነቱ ለ40 ቀናት የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በዚህ ወቅት ሀማስ ያልቀቃቸውን 100 የእስራኤል ታጋቾች እንዲለቅ ሀሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።
በቀጣዩ ዙር ደግሞ የእስራኤል ወታደሮች እና የሞቱ ሰዎች አስከሬን ማስረከብ እንደሚኖር ዘገባው ጠቅሷል።
ይህ የረጅም ጊዜ የተኩሴ አቁም ሀሳብ፣ ሃማስ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 240 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ የመጀመሪያው ነው።
ባለው ህዳር በኳታር አደራደሪነት እስራኤል እና ሀማስ በደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ሀማስ በርካታ ታጋቾችን ሲለቅ በምላሹ እስራኤል ፍልስጤማውያን እስረኞችን መልቀቋ ይታወሳል።
ለስድስት ቀን የቆየው ይህ ተኩስ አቁም ከተጣሰ በኋላ የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
እስራኤል ተኩስ እንድታቆም ጫና ቢደረግባትም፣ ሀማስን የማጥፋት እቅዷ ግብ ሳይመታ እንደማታቆም መግለጿ ይታወሳል።
እስራኤል በደቡብ አፍሪካ የዘርማጥፋት ክስ ቀርቦባት በአለምአቀፍ ፍርድ ቤት ቀርባ እየተከላከለች ትገኛለች።