አሜሪካ የህወሓት ሀይሎች በትግራይ ክልል ባሉ የኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እንዳሳሰባት ገለጸች
በትግራይ ክልል በማይ አይኒ እና አዲ ሀሩሽ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች 24 ሺህ ኤርትራዊያን ስደተኞች አሉ
በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የታጠቁ ሀይሎች ጥቃት እንደተጋለጡ ነው- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት
አሜሪካ በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የህወሓት ታጣቂዎች እየፈጸሙት ያለው ጥቃት እንዳሳሰባት ገለጸች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ስለመሆኑ አሳማኝ መረጃ አልኝ ብሏል።
በተለይም በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች ካምፖች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ስለመሆናቸውም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የታጠቁ አካላት በኤርትራዊያን ስደተኞች፣ ጥገኝነት በጠየቁ አካላት እና በግጭቱ ሳቢያ በተፈናቀሉ ሰዎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል።
እንዲሁም በክልሉ የሰባአዊ ድጋፍ ለማድረስ በሚንቀሳቀሱ የሰብኣዊ ድርጅት ሰራተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠይቋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኖች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያው አይደለም ያለው መግለጫው፤ ከዚህ ቀደም በጥር ወር ላይ በስደተኞቹ ላይ ግድያ ጨምሮ አፈና እና በግዳጅ ለኤርትራ የጸጥታ አካላት አሳልፎ የመስጠት ተግባራት መፈጸማቸውን አስታውቋል
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አካላት በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት አያያዛ ህግ መሰረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጹ የጠየቀው ሚኒስቴሩ፤ በተግባሩ የተሳተፉ አካላትም ተጤቅ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርቧል።
በተመሳሳይ በትግራይ ያሉ የኤርትራ ስደተኞች በታጠቁ ሀይሎች ጥቃት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን የተባሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች የታጠቁ ሀይሎች ጥቃት እንደተጋለጡ ነው።
በትግራይ ክልል በማይ አይኒ እና አዲ ሀሩሽ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች 24 ሺህ ኤርትራዊያን ስደተኞች ያሉ ሲሆን በሰሜን አትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለደህንነታቸው ስጋት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
በተለይም ከሰሞኑ በማይጸብሪ እና አካባቢው ውጊያ መኖሩን ተከትሎ ስደተኞቹ ስጋት ውስጥ መውደቃቸው ተገልጿል ተገልጿል።
በዚህ ውጊያ ምክንያት የተመድ የስደተኞች ድርጅቶች ተንቀሳቅሰው ለስደተኞቹ ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውን ተመድ አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ባባር ባሎሽ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ አስደንጋጭ ሪፖርቶች እየደረሷቸው መሆኑን ገልጸው፤ በማይ አይኒ ስደተኞች መጠለያ አንድ ስደተኛ መገደሉን እና በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የጦር መሳሪያ መተከሉንም በስጋት አነስተዋል።
ይሁንና ለዚህ ድርጊት ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ከመናገር የተቆጠቡት ቃል አቀባዩ፤ የታጠቁ ሀይሎች በሁለቱ ስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ስደተኞቹ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የሰብአዊ መብት ድጋፎችን እያገኙ አለመሆነ የተጠቀሰ ሲሆን መንግስት ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጥ በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
አሁንም ጦርነቱ መቀጠሉ እንዳሳሰበው የገለጸው ድርጅቱ በአፋር በኩል ነዋሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት መኖሪያ ቀዬአቸውን በመልቀቅ ላይ ሲሆኑ ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል ከ55 ሺህ በላይ ያህሉ ኤርትራዊያን እንደሆኑ ተገልጿል።