በኤርትራ ስደተኞች ላይ በሚደርሱ “የሰብአዊ መብት ጥሰቶች”ሪፖርት መጨነቁን ተመድ ገለጸ
ኤጀንሲው በግጭቱ ተሳታፊዎች የኤርትራ ስደተኞች ተለይተው ኢላማ ተደርገዋልም ብሏል
ኤጀንሲው በማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠሊያ ጣብያዎች የሚገኙት 24 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ቀጣይ እጣ ፈንታ ያሳስበኛል ማለቱ የሚታወስ ነው
ሁሉም ተዋጊዎች የኤርትራ ስደተኞችን ደህንነት እንዲጠብቁ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
በትግራይ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በክልሉ ተጠልለው የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች በውግያ መሃል እንደሚገኙና በሁለቱም ኃይሎች ዒላማ እየተደረጉ መሆናቸውን በኤርትራ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ላይ የተባበሩት መንግስታት ልዩ ዘጋቢ ዶ/ር መሀመድ ዓብዱልሰላም ባቢከር ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር መሀመድ ዓብዱልሰላም ሁሉም የጦርነቱ ተዋናዮች ለዓለም አቀፍ ህግና ሰብዓዊ መብቶች ተገዥ በመሆን የስደተኞችን ደህንነት ሊጠብቁ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ግጭት ከመከሰቱ በፊት በትግራይ ክልል 100 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ይኖሩ ነበር ያሉት ባቢከር ፤ ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ የስደተኞቹ ድህንነት እንዲጠበቅ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ መንግስታት ባለፉት የካቲት እና ሰኔ ወራት መምከራቸውንም አስታውሷል፡፡
“ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ በኤርትራ ስደተኞች ላይ ቢአትዮጵያ መንግስት፣ በኤርትራ ኃይሎች እና ከህወሓት ጋር ግንኙነት ባለቸው ኃይሎች የተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ ሕግ ጥሰቶች በተመለከተ ተዓማኒነት ያላቸው ክሶች ደርሰውኛል”ም ነው ያሉት የተባበሩት መንግስታት ልዩ ዘጋቢው ዶ/ር መሀመድ ዓብዱልሰላም ባቢከር፡፡
ባቢከር አክለው “በግጭቱ ውስጥ ከሁለቱም ወገን የኤርትራ ስደተኞች ተለይተው ኢላማ ተደርገዋል እንዲሁም ተጎጂ ሆነዋል”ም ብሏል፡፡
አሁን ግጭቱ እየተስፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ 80 ሺህ የሚሆኑ በትግራይና አፋር ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
“የኤርትራ ስደተኞችን በተመለከተ እየደረሱኝ ባሉ የበቀል ጥቃቶች እና ግድያዎች ፣ የወሲባዊ ጥቃት፣ የኤርትራ ስደተኞች ድብደባ እንዲሁም የመጠሊያ ጣብያዎች እና ንብረቶች ዘረፋን ሪፖርቶች ተጨንቄአለሁኝ:: በስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት መቆም አለበት” ዶ/ር መሀመድ ዓብዱልሰላም ባቢከር፡፡
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሺ ባሳለፍነው ሃምሌ ወር መጨረሻ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠሊያ ጣብያዎች የሚገኙት 24 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ቀጣይ እጣ ፈንታ ያሳስበኛል ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የኤርትራ ስደተኞችን ይኖሩባቸው የነበሩ የህጻጽ እና ሽመልባ መጠሊያ ጣብያዎች መውደማቸው፣ 20ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች መፈናቀላቸው እንዲሁም በመቶወች የሚቆጠሩ ድበዛቸው መጥፋቱ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ግጭቱ ወደ ከትግራይ ባሻገር ወደ ክልሎች በመስፋፋቱ 55ሺህ የኤርትራ ስደተኞች በሚገኙባት አፋር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውም የሚታወቅ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብአዊነት ሕግ በግጭት ውስጥ የተያዙ ዜጎችን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን እውቅና ከሰጠ ቆይተዋል፡፡