የገና በዓል እና በመላው አለም የሚገኙ ለየት ያሉ የአከባበር ባህሎች
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ሀገራት በዛሬው ዕለት ገናን እያከበሩ ነው
ኢትዮጵያ ፣ ሩስያ፣ ግብጽ፣ ኤርትራ እና ግሪክን የመሳሰሉ ሀገራት በዓሉን በታህሳስ 28 ወይም 29 በጋራ ያከብራሉ
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የእየሱስ ክርስቶስ ልደትን በማስመልከት የሚከበረው የገና በዓል በመላው አለም በድምቀት ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ ክብረ በአሎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በዓሉ እንደየአካባቢው እና እንደየባህሉ የተለያዩ መገለጫዎች አሉት። ከሀይማኖታው ክዋኔዎች ጎን ለጎን በአሉ የሚቃኝባቸው ትውፊታው መገለጫዎች የተለየ መልክ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
በገና ዛፍ መኖርያቤቶችን እና መንገዶችን ማሸብርቅ ፣ ስጦታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችን መለዋወጥ በርካታ የክርስትና እምነት ተካታዮች የገና አከባበር ከሚመሳሰሉባቸው መገለጫዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአሜሪካ ብቻ 3 ቢሊየን የገና መልካም ምኞት መግለጫ ካርዶች በየአመቱ ይላካሉ፤ በተመሳሳይ በአመት 35 ሚሊየን የገና ዛፎች ለሽያጭ የሚቀርቡ ሲሆን 45 ሚሊዮን የገና ዛፍ ችግኞች ደግሞ ይተከላሉ፡፡
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ሀገራት በዛሬው ዕለት ገናን የሚያከብሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ፣ ሩስያ ፣ ግብጽ፣ ኤርትራ እና ግሪክን ጨምሮ 14 ሀገራት በዓሉን በታህሳስ 28 ወይም 29 በጋራ ያከብራሉ።
ለየት ያለ የገና በአል አከባበር ያላቸው የአለም ሀገራት
-ፖላንድ
ለየት ያለ ባህላዊ የገና ባዓ አከባበር ካላቸው ሀገራት መካከል ፖላንድ አንዷ ናት። ሀገሪቱ በአሉን ከቁሳዊ እና ከስጦታ መለዋወጥ ትኩረት ለማውጣት በተለያዩ ጊዜ ጥረቶችን አድርጋለች፡፡
በዚህም ቤተሰቦች ስጦታ የሚለዋወጡት በበዓሉ ዋዜማ ሲሆን በዋዜማው እኩለ ሌሊት ላይ ወደ አብያተ ክርስቲያናት በማቅናት ሀይማኖታዊ ስነስርአቶችን ይታደማሉ፡፡
በዓአሉ ቀን አስራ ሁለቱን የእየሱስ ክርስቶስ ሀዋርያት ለማሰብ 12 አይነት ምግብ በማዘጋጀት ቤተሰቦች በአንድ ማዕድ ላይ ተሰባስበው ያሳልፉታል፡፡
- ፊሊፒንስ
እስያዊቷ ሀገር ገናን በተለየ ሽብርቃ እና ማስዋብ ከሚያከብሩ ሀገራት ዘንድ ትመደባለች። ሳን ፈርናንዶ የተባለው ከተማ የገና መዲና በመባል ይታወቃል፡፡
በዚች ከተማ ከሌሎች የፊሊፒንስ ተሞች በተለየ የገና ገበያዎች እና ቬስቲቫሎች የሚደምቁበት ሲሆን ከሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በዚች ከተማ በዓሉን ለመታደም ፍሊፕናዊን ይጎርፋሉ፡፡
ከተማዋ ከምትታወቅባቸው መለያዎች መካከል ሰብዓሰገል የእየሱስን መወለድ ለማብሰር ተከትለውት የመጡትን የቤተልሄም ኮከብ አምሳያ በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ ላይ በመስቀል የምታሳየው አመታዊ የብርሀን ትርዒት አንዱ ነው።
-ሜክሲኮ
ከፈረንጆቹ ታህሳስ መጀመርያ አንስቶ በተለያዩ የአደባባይ ትዕይንቶች እና ትርኢቶች ማክበር የምትጀምረው ሜክሲኮ ዋናው በአል እስከሚከበር ድረስ የሚቀጥሉ አመታዊ ሁነቶችን ታዘጋጃለች፡፡
በቤት ውስጥ እና በአደባባይ በየአመቱ የሚካሄዱ ፌስቲቫሎች በርካታ ተመልካቾችን እና ጎብኝዎችን መሳብ የቻሉ ናቸው፡፡
ከነዚህ ትርኢቶች መካከል የእየሱስን መወለድ የሰሙት እረኞችን ሁኔታ እንዲሁም ጌታን የጸነሰች ማርያም ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ያደረገችውን ስደት የሚያሳዩ ትርኢቶችን ያቀርባሉ፡፡
በበአሉ ዋዜማም ዋና ዋና መንገዶች በገና ማሸብረቂያዎች እና አበቦች ይዋባሉ፡፡
- ጓቲማላ
በጓቲማላ አዲስ አመት እና የእየሱስ ክርስቶስን መወለድ ከመከበሩ በፊት የመጥፎ መንፈስን ማስወገድ ወሳኝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
በዚህም ሰይጣን እና መጥፎ መንፈስ ይኖርበታል ብለው የሚያስቡትን የቤታቸውን ማዕዘናት የተቀጣጠለ ልዩ እንጨት በመያዝ ዙርያውን ይሽከረከራሉ፡፡
ቀጥሎም የገና ጽዳትም ሆነ የምግብ ዝግጅት የሚደረገው ይህ ባህላዊ ክዋኔ ከተፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በተለምዶ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን አሰባስበው ከወላጆቻቸው ጋር የማሳለፍ ልምድ አላቸው፡፡
በገጠሩ አካባቢ የሚገኙ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሰዎች አመቱን በሙሉ ለገና በአል የሚያስፈልጉ ምግብ እና መጠጦችን እንዲሁም ሌሎች ማስጌጫዎችን ለመግዛት ሲቆጥቡ ይከርማሉ፡፡
ዋናው የበአሉ ምግብ ለመብል የሚቀርበው በበአሉ ዋዜማ ምሽት ሲሆን በዚህ ወቅት ጣፋጮች ፣ የዶሮ እና የሌሎች እንስሳት ተዋጽዖ ምግቦች ለመብልነት ይቀርባሉ፡፡