በቱርክ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰራተኞች አሉ
ቱርክ ዝቅተኛ የሰራተኛ ደመወዝ ወለልን ወደ 630 ዶላር አሳደገች፡፡
በፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የሚመራው የቱርክ መንግስት ዝቅተኛ የሰራተኞች ደመወዝ 630 ዶላር እንዲሆን ወስኗል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2025 ጀምሮ የሚተገበር ዝቅተኛ የሰራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ተወስኗል፡፡
ዘጠን ሚሊዮን ሰራተኞች ያሏት ቱርክ ዝቅተኛ ወርሃዊ ደመወዝ 22 ሺህ ሊራ ወይም 630 ዶላር እንደሚሆን ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ተናግረዋል፡፡
ቱርክ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካለባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን አሁን ላይ የኑሮ ውድነቱ 47 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የሀገሪቱ አማካኝ የዋጋ ግሽበት መጠን 75 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ሲሆን ይህም ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል ተብሏል፡፡
የቱርክ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ሊራ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለው ልዩነት እየጨመረ መምጣት ለዋጋ ንረቱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ35 የቱርክ ሊራ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
ቱርክ ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ስትሆን በ2025 አንድ ሚሊዮን መኪኖችን ለመሸጥ ማቀዷን ገልጻለች፡፡