ብሪታንያዊው ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ ዩናይትድን ለመግዛት ፉክክሩን ተቀላቀሉ
ከ6 ቢሊየን ፓውንድ በላይ የሚገመት ሃብት ያላቸው ራትክሊፍ፥ የሚደግፉትን ክለብ በስንት ፓውንድ እንደሚገዙ ግን ይፋ አላደረጉም
ሌዘር ቤተሰቦች በህዳር ወር 2022 ማንቸስተር ዩናይትድን የመሸጥ ሃሳብ ማቀረባቸው ይታወሳል
ብሪታንያዊው ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ ማንቸስተር ዩናይትድን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።
የቢሊየነሩ ኩባንያ ኢኒዮስ ዩናይትድን ለመግዛት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ መግባቱን ይፋ አድርጓል።
የግሌዘር ቤተሰቦች በህዳር ወር 2022 ማንቸስተር ዩናይትድን የመሸጥ ሃሳብ ማቀረባቸውን ተከትሎ ነው ቢሊየነሩ ፍላጎታቸውን የገለጹት።
ቼልሲን በ4 ነጥብ 25 ቢሊየን ፓውንድ ከሩሲያዊው ባለሃብት ሮማን አብራሃሞቪች ለመግዛት ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ያጣው ራትክሊፍ፥ የማንቸስተሩን ክለብ በእጃቸው ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።
ቼልሲን ለመግዛት ካደረጉት ጥረት አለመሳካት በኋላ የግሌዘር ልጆችን ጆየል እና አቭራም ግሌዘር በማግኘት ዩናይትድን ለመግዛት ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል።
የክለቡ ባለቤቶች በሂደት ሃሳባቸውን በመለወጣቸው ግን ሰር ጂም ራትክሊፍ ዳግም ሂደቱን መቀላቀላቸውን ነው ስካይ ኒውስ ያስነበበው።
በማንቸስተር ተወልደው ያደጉት ሰር ጂም ራትክሊፍ፥ ከልጅነታቸው ጀምሮ የቀያዮቹ ሰይጣኖች ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው።
ብሪታንያዊው ቢሊየነር ሃብታቸው በፎርብስ 11 ቢሊየን ፓውንድ፤ በሰንደይ ታይምስ ደግሞ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ተገምቷል፤ ይህም 27ኛው የሀገሪቱ ባለጠጋ ያደርጋቸዋል።
ዩናይትድን እንደሚገዛ ያስታወቀው የነዳጅ ኩባንያቸው ኢኒዮስ በአመት የ50 ቢሊየን ፓውንድ ሽያጭ የሚያካሂድ ሲሆን፥ በ29 ሀገራት ከ26 ሺህ በላይ ሰራተኞች አሉት።
ኩባንያው የፈረንሳይ ሊግ 1 ክለቡ ኒስ እና የስዊዘርላንዱን ክለብ ላውሳን ባለቤት ነው።
ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ ዩናይትድን ገዝተው የሚያስተዳድሩት የግሌዘር ቤተሰቦች ከደጋፊዎች የሚቀርብባቸው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሲመጣ ባለፈው ህዳር ወር ክለቡን ለመሸጥ ማሰባቸውን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።