የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአፋጣኝ ቆሞ ወደ ውይይት መገባት አለበት- የፀጥታው ም/ ቤት
የተናጠል የማዕቀብ እርምጃዎችን የተቃወሙት ቻይናና ሩሲያ፤ የኢትዮጵያን መንግስት መደገፍ ይገባል ብለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት የተመድ ሰራኞች ከሀገር እንዲወጡ ያሳለፈውን ውሳኔ ሊቀለብስ ይገባል- አሜሪካ
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ከልል ባለው ጉዳይ ላይ በዛሬው እለት ተወያይቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች 7 ሚሊየን ሰዎች ምግብ እና ሌሎችም የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ ሰብአዊ ድጋፎች በሚፈለገው መጠንም እየደረሱ አይደለም ሲሉም ተናረግረዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ጦርነትም ሌላኛው የሰብአዊ ቀውስን ያስከተለ ነው ያሉት ዋና ፀሃፊው፤ በሁሉም ወገን እየተፈፀመ ያለው ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም አሳሳቢ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት 7 የተመድ ሰራኞችን ከሀገር እንዲወጡ ማዘዙ አሳሳቢ ነው ያሉ ሲሆን፤ “ያልተጠበቀ” ያሉት የሰራተኞቹ መባረር ለሁሉም አሳሳቢ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ለተመድ ማሳወቅ ነበረባት፤ እርምጃው አስፈላጊ ከሆነም መከተል የነበረባት ሂደቶች ነበሩ፤ ግን አልተጠበቁም ብለዋል።
ተመድ ለተቸገሩ ሰዎች ለመድረስ እንዲችል የኢትዮጵያ መንግስት ቪዛን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲያሟላም ጠይቀዋል።
ከሁለት ቀን በፊት የተመሰረተው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት ጠንካራዋን ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ ያሉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉን አካታች ውይይት ለማድረግ የገቡትን ቃልም አደንቃለሁ ብለዋል።
ብሪታኒያ ፣ኢስቶኒያ ፣አየርላንድ፣ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ ኢትዮጵያ የተመድ ሰራተኞችን ማባረር አልነበረባትም ያሉ ሲሆን፤ ፈረንሳይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉን አካታች ውይይት ለማስጀመር ለወሰዱት ኃላፊነት ድጋፍ አለኝ ብላለች።
የአሜሪካ ተወካይ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት 7 የተመድ ሰራኞችን ከሀገር እንዲወጡ ያሳለፈው ውሳኔ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህንን ላደረገችበት ምንያት ምንም አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አትችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስ ይገባል ያለችው አሜሪካ፤ በጦርነቱ ላይ የተካፈሉ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አጠቃላይ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱም ጠይቀዋል።
ይህ የማይሆን ከሆን ግን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምር ቤት በአፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የቻይና ተወካይ ተመድ እና የተመድ ሰራተኞች የተቋሙን መርህ ተከትለው ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርሱ ይገባል፤ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካላት ለመድረስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለኢትዮጵያ መንግስት ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፎችን ለማድረስ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ላለው ስራ ቻይና እውቅና በመስጠት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሀገር ለሚገቡ ሰራተኞች የቪዛ ሂደቶችን ማቅለሉን፣ የፍተሸ ጣያዎች ቁጥርን መቀነሱን እና የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች አስፈላጊውን የተግባቦት መሳሪያ እንዲያስገቡ መፍቀዱንም አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ እና ድጋፎች እንዲደርሱ ለማድረግ ያለው ብቸኛ አማራጭ ዲፕሎማሲያው መንገድ ብቻ ነውም ብለዋል።
ቻይና አዲስ ለተመሰረተው መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻ፤ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ይህንን እንዲያድርግ ጠይቃለች።
ቻይና አክላም አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የተናጠል ማዕቀብ ለመጣል ማሰባቸው ዓለም አቀፍ ህግን መጣስ መሆኑን አስታውቃለች። በመሆኑም አስመራ እና አዲስ አበባ የተጣሉ ማዕቀብ በአስቸኳይ ሊነሳ ይገባል ብላለች።
በተመድ የሩሲያ ተወካይም በተናጠል የሚወሰዱ የማዕቀብ እርምጃዎች ችግሩን እንደሚያባብሱ በመግለፅ ተቃውመዋል ።
ሀገራቸውም ለኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹ ሲሆን የግጭቱ መፍትሄ ፓንአፍሪካዊ በሆነ መንገድ ይሆን ዘንድ አቋማችን ነው ብለዋል ።
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር መፍታት የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ሩሲያ ታምናለች። አለማቀፉ ማህቀረሰብም ይህንኑ ከግምት ሊያስገባው አስፈላጊ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሰት በሚያደርገው የመፍትሄ ተግባራት ውስጥ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ከጎኑ ሊሆን ይገባዋል። ቀውሱን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ የተቀናጀ ትብብር መሆኑን በአፅንኦት እንገልፃለን ብለዋል።
አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ ሀገራት የተለያዩ የተመድ ሰራተኞችን እና የሀገራት ዲፕሎማቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው ማስወጣታቸውን እናውቃለን፤ ሆኖም ግን ተመድ በእነሱ ላይ ስብሰባ አድርጎ ያውቅ ይሆን ሲሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃውን ስለ መውሰዱ ለማንኛውም አካል ማብራሪያ የመስጠት ግዴታ የለባትም ብለዋል።
የተመድ ሰራተኞች የገለልተኝነት መርሆችን በጣሰ መልኩ ለህወሓት የሚወግኑ መሆናቸውን በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አክለው ገልጸዋል።
አምባሳደር ታዬ የተመድ ሰራተኞች ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል በሚል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት፤ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ወገን ማድረስ፤ ህወሃት መቀሌ ሲገባ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን መግለጽ፤ ከሳዑዲ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሦሥተኛ ሀገር በማምጣት ለቡድኑ እንዲዋጉ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ህወሓትን የሚደግፉ ጹሑፎችን ማዘገጀት ላይ ተጠምደው ነበር ብለዋል።
ጉቴሬስ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ስለተባረሩ የተመድ ሰራኞች የደረሰኝ አንድም ማስረጃ የለኝም፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን ጥሳ ነው ይህንን ተግር እርምጃ የወሰደችው ብለዋል።
ጉቴሬስ፤ “እኛ በኢትዮጵያ ላይ ሌላ አጀንዳ የለንም፤ እኛ ያለን አጀንዳ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በተመድ እና በኢትዮጵያ መካከል ባቻ በንግግር መፈታ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተባረሩ የተመድ ሰራተኞች ላይ አስፈካጊውን ማስረጃ እንደሚያስገቡ አስታውቀዋል።