“የተመድ ጸጥታው ም/ቤት በግድቡ ላይ የመወሰን ስልጣን የለውም”- የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አምባሳደሮች
ግድቡን ወደ ተመድ መውሰድና አረቦችን ማሳመን አግባብ እንዳልነበረም ተገልጿል
ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሯን ግብፅ መግለጿ ይታወሳል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ግድቡ የልማት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን እንደሌለው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አምባሳደሮች አስታወቁ።
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት እነዚህ አምባሳደሮች ዛሬ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።
አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያሉ አዳዲስ ክስተቶችን በተመለከተ ለተደራዳሪ ሀገራት መረጃ ማጋራቷን ማድነቃቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ዲፕሎማቶቹ የግድቡን ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተሉትና ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ወደፊት ዓባይን ለልማት የማዋል ራዕይ እንዳላቸው ተገልጿል።
የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት መካሄዱ በጎ መሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቶቹ፤ ወንዙ እና የተፋሰሱ ሀገራት የአፍሪካ በመሆናቸው በሕብረቱ ጥላ ስራ የተጀመረው ድርድር መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ተደራዳሪ ሀገራት በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት እየተካሄደ ባለው ድርድር ሰላማዊ መፍትሔን መምረጥ እንዳለባቸውም የተገለጸው፡፡ ይህንን በማድረግም ለአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን መፈለግን ማበረታታት እንደሚገባ አንስተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ግድቡ የልማት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን እንደሌለውም አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ግድብ በሚመለከት ግብፅ እና ሱዳን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት መውሰዳቸው አላስፈላጊ መሆኑን ገልጸውላቸዋል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም አረቦችን ከጎን ማሳለፍም ትክክል እንዳልሆነ አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
ግብፅ ትናንትናው እለት ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሯን እንደነገረቻት መገለጹ ይታወሳል።