በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት የነበረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዴት ሊከሰት ቻለ?
የቀጣይ ክረምት ወራት የዝናብ መጠንስ ምን ሊመስል ይችላል?
በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ ታሪክ በሶማሌ ክልል ቀብሪደሀር በ24 ሰዓት ውስጥ የዘነበው ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል
በኢትዮጵያ ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ ቦታዎች ክረምት በሚመስል መልኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነብ ላይ ይገኛል።
እንደ ኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ከሆነ ያለፉት ሶስት ወራት የኦሮሚያ ክልል ደቡባዊ ክፍል፣ ደቡብ ሶማሊ እና ከደቡብ ክልል ደግማ ደቡባዊ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ የሚያገኙባቸው ወቅቶች ናቸው።
በእነዚህ አካባቢዎች ከአምስት ወቅቶች በኋላ ዝናብ መዝነቡ መልካም እና የሚጠበቅ ቢሆንም በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ባልሆኑ ቦታዎችም ጭምር ዘንቧል ተብሏል።
አልዐይን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የስራ ሃላፊ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኢንስቲትዩቱ የረጅም ጊዜ ትንበያና ድርቅ ክትትል ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሙሉአለም አበረ፥ በዘንድሮው የበልግ ወቅት ለምን ከፍተኛ ዝናብ ሊዘንብ እንደቻለ አብራርተዋል።
ድሬዳዋ፣ ደቡብ እና ሰሜን ወሎ፣ ኮንሶ፣ ጅንካ፣ ጭፍራ እና ደቡብ ሶማሌ አካባቢዎች በቀን 100 ሚሊ ሜትር ዝናብ እያገኙ ነው ብለዋል።
የበልግ ዝናብ ከሚዘንብባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ በሌሎችም አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንዲዘንብ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በህንድ፣ አትላንቲክ እና ፓስፊክ ውቂያኖሶች እርጥበታማ አየር ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን በዋና ምክንያትነት ሀላፊው ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከዝናቡ በተጨማሪ ከፍተኛ ሙቀትም በመኖሩ እና በዚህ ምክንያት ትነትን ተከትሎ የዳመና መጠኑ መጨመሩ ለዝናብ መብዛት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።
በቀብሪደሀር በ24 ሰዓት ውስጥ 230 ሚሊ ሜትር ዝናብ መዝነቡን ያነሱት አቶ ሙሉዓለም ይህ አሀዝ በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ መጠን ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በ24 ሰዓት ውስጥ 30 ሚሊ ሜትር ዝናብ እና ከዛ በላይ ሲዘንብ ከፍተኛ ዝናብ ዘንቧል ተብሎ የሚመዘገብ ሲሆን ቀብሪደሀር፣ ዳሊፋጊ እና አዲስ አበባ በበልጉ ወቅት ከ70 እስከ 230 ሚሊሜትር ዝናብ የዘነበባቸው ቦታዎች ናቸው ተብሏል።
ከዛሬ ጀምሮም ከደቡብ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ሶማሊ፣ ደቡብ ክልል ደቡባዊ ክፍል በስተቀር ክረምት መግባቱን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
እንዲሁም መካከለኛው ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ክልል ሰሜናዊ ክፍል፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ፣ አፋር ክልል፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ሶማሌ ክልል ሰሜናዊ ክፍል በክረምቱ ወራት ውስጥ መደበኛ እና ከዛ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያው ያስረዳል።
ምዕራብ አማራ ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛ እና ከዛ በላይ ዝናብ ያገኛሉም ተብሏል።
የዘንድሮው ክረምት ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ መውጣት እንደሚጀምር የገለጹት አቶ ሙሉዓለም ሰሜን ኢትዮጵያ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ ደግሞ ክረምቱ ቀድሞ የሚወጣባቸው አካባቢዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በበልግ ወቅት መደበኛ እና ከዚያ በላይ ዝናብ ማግኘታቸውን ተከትሎ በክረምቱ ወቅትም ዝናቡ ሲቀጥል የጎርፍ እና መሬት መንሸራተት አደጋዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በስጋትነት ተቀምጧል።