በብራዚል በጣለ ከባድ ዝናብ የ36 ሰዎች ህይወት አለፈ
በአደጋው ምክንያት ከተሞች የአደባባይ በዓላትን ሰርዘዋል ተብሏል
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ አካባቢውን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል
በብራዚል በጣለ ከባድ ዝናብ የ36 ሰዎች ህይወት አለፈ
በብራዚል ሰሜናዊ ክፍል ሳኦ ፓውሎ ግዛት የጣለው ከባድ ዝናብ ባደረሰው የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት የ36 ሰዎች ህይወት ማለፉን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ባለስልጣናቱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የሳኦ ፓውሎ ግዛት መንግስት በሳኦ ሰባስቲኦ ከተማ 35 ሰዎች መሞታቸውን እና በአጎራባች ኡባቱባ ደግሞ የሰባት ዓመት ሴት ልጅ ህይወት ማለፉን አስታውቋል።
ሳኦ ሰባስቲኦ፣ ኡባቱባ፣ ኢልሃቤላ እና ቤርቲዮጋ የተባሉ ከተሞች በጣም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ተብሏል።
ከተሞች የነፍስ አድን ቡድኖች በችግር ውስጥ ላሉ፣ በፍርስራሹ ውስጥ የጠፉትና የተጎዱ ሰዎች ለማግኘት በሚያደርጉት ትግል የአደባባይ በዓላቸውን ሰርዘዋል ሲል የአሜሪካው ኤንፒአር ዘግቧል።
የሳኦ ሰባስቲኦ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ፌሊፔ አጉስቶ "የእኛ የነፍስ አድን ቡድኖቻችን ወደተለያዩ ቦታዎች ለመድረስ እየቻሉ አይደለም፤ ሁኔታው ምስቅልቅል ያለ ነው" ብለዋል።
በኋላም በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች የጠፉ መሆናቸውን እና በከተማዋ 50 ቤቶች በቆሻሻ መደርመስ ሳቢያ መፍረሳቸውን አሳውቀዋል።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ በትዊተር ገጻቸው አካባቢውን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል። ነዋሪዎች እቃዎቻቸውንና ሰዎችን ወደ ከፍተኛ ቦታዎች ለማጓጓዝ ትናንሽ ጀልባዎችን እየተጠቀሙ ነው።
ሪዮ ዴ ጄኔሮን ወደ ወደብ ከተማዋ ሳንቶስ የሚያገናኘው መንገድ በመሬት መንሸራተትና በጎርፍ ተዘግቷልም ተብሏል።