አሜሪካ በበኩሏ ወታደሮቿ በእስራኤል ቢኖሩም ከሀማስ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት ውስጥ እንዳልተሳተፈ አስታውቃለች
የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ ባሳለፍነው እሁድ ዋሸንግተን በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት በጋዛ እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል ጥቃት በመቃወም ራሱን ማቃጠሉ ይታወሳል፡፡
አሮን ቡሽነል የተባለው የ25 ዓመቱ የአሜሪካ አየር ሀይል አባል ወታደር በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ምክንያት ህይወቱ አልፏል፡፡
ግለሰቡ "በዘር ማጥፋት አልተባበርም" ሲል ወታደራዊ ልብስ ለብሶ ራሱን ሲያቃጥል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቀጥታ ስርጭት ተላልፏል።
ዘግይተው በወጡ ዘገባዎች ይህ ወታደር የሀገሩ አሜሪካ ወታደሮች በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት እየተሳተፉ እንደሆነ ማወቁ ራሱን ለማጥፋቱ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ኒዮርክ ፖስት እንደዘገበው አሮን ቡሽነል በጋዛ የሐማስ ዋሻዎች ውስጥ የአሜሪካ ወታደሮች እየተዋጉ እንደሆነ እና በርካታ ፍልስጤማዊያንን እንደገደሉ ያውቃል ተብሏል፡፡
የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የተገለጸ አንድ የአሜሪካ ወታደር በእስራኤል ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች ከእስራኤል ጦር ጋር በመሆን ወደ ጋዛ እንደገቡ እና በውጊያ እየተሳተፉ እንደተነገረው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካ አየር ኃይል አባል በዋሽንግተን በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊትለፊት ራሱን አቃጠለ
የአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ የደህንነት ባለሙያ የሆነው አሮን ሀገሩ በዘር ማጥፋት ወንጀል መሳተፏን መቀበል አቅቶት ራሱን ሊያጠፋ ችሏልም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግስት በበኩሉ የአሜሪካ ወታደሮች በጋዛ እየተደረገ ባለው የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት አልተሳተፉም ሲል አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በያዝነው ሳምንት እስራኤል እና ሐማስ ጦርነቱን ለማስቆም የሰላም ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋልም ተብሏል፡፡
ከአምስት ወር በፊት ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የአሜሪካ ልዩ ወታደሮች ወደ እስራኤል ቢጓዙም ወደ ጦርነቱ እንዳልገቡ ተገልጿል፡፡