የአሜሪካ አየር ኃይል አባል በዋሽንግተን በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊትለፊት ራሱን አቃጠለ
ጉዳዩን የአካባቢው ፖሊስ እና ሰክሬት ሰርፊስ እየመረመሩት ነው ተብሏል
የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ ራሱን ያቃጠለው በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቃወም መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል
የአሜሪካ አየር ኃይል አባል በዋሽንግተን በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊትለፊት ራሱን አቃጠለ።
የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ በትናትናው እለት በአሜሪካ በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ፊት ለፊት ራሱን ያቃጠለው በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቃወም መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሰክሬት ሰርቪስ አባላት እሳቱን ካጠፉለት በኋላ የአየር ኃይል አባሉን ወደ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዋሽንግተን ፖሊስ ዲፖርትመንት ቃል አቀባይ እንደገለጹት ግለሰቡ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። የአየር ኃይሉ ቃል አቀባይ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ በስራ ላይ የነበረ አባል እንደነበር አረጋግጠዋል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ግለሰቡ "በዘርማጥፋት አልተባበርም" ሲል ወታደራዊ ልብስ ለብሶ በቀጥታ በኦንላይን መልእክት አስታልፏል።
ይህን ካለ በኋላ ግለሰቡ ሰውነቱ ላይ ፈሳሽ ደፍቶ እሳት በመለኮስ "ነጻ ፍልስጤም" የሚል የለቅሶ ድምጽ አሰምቷል ብሏል ዘገባው።
ጉዳዩን የአካባቢው ፖሊስ እና ሰክሬት ሰርፊስ እየመረመሩት ነው ተብሏል።
በዋሽንግተን የሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት የሚቃወሙ ሰልፎች የሚካሄዱበት ቦታ ሆኗል። እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ያለው ጦርነት በአሜሪካ እስራኤልን የሚደግፉ እና ፍልስጤምን የሚደግፉ ሰልፎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል።
ተቃውሞዎቹ የተጀመሩት በፈረንጆቹ 2023 ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ እገታ እና ግድያ ከፈጸመ በኋላ ነው።
እስራኤል በሀማስ ላይ እየወሰደችው ባለው እርምጃም እስካሁን 30 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ባለፈው ታህሳስ ወር በአትላንታ በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ ፊት ለፊት አንድ ተቃዋሚ ራሷን በእሳት ማያያዟን ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ እያደረገችው ያለው ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በመፍጠሩ በርካታ ሀገራት እና ተመድ ተኩስ እንዲቆም ይፈልጋሉ።
ነገርግን እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ሀማስ ከምድረ ገጽ መጥፋቱ ሳይረጋገጥ ተኩስ እንዲቆም አይፈልጉም።