አሜሪካ በሶማሊያ የአይኤስ ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ገለጸች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በዋሻዎች የተደበቁ የአይኤስ ታጣቂዎች ለአሜሪካ እና አጋሮቿ ደህንነት ስጋት ሆነዋል" ብለዋል
ሶማሊያ በአሜሪካ የተፈጸመው የአየር ድብደባ የሞቃዲሾ እና ዋሽንግተን ጠንካራ የጸረ ሽብርተኝነት ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጻለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ በሚገኘው የአይኤስ የሽብር ቡድን ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት እንዲፈጸም ማዘዛቸውን ተናገሩ።
ትራምፕ "እነዚህ በዋሻዎች ውስጥ የተደበቁ ገዳዮች የአሜሪካ እና አጋሮቿ ደህንነት ስጋት ሆነዋል" ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በአየር ጥቃቱም የተደበቁባቸው ዋሻዎች መውደማቸውንና በንጹሃን ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መገደላቸውን ጠቁመዋል።
በአየር ጥቃቱ ኢላማ የተደረጉ የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች ስምም ሆነ የተገደሉትን አሃዝ ግን አልጠቀሱም።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ አሜሪካ በሰሜናዊ ሶማሊያ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ዙሪያ አስቀድማ ለሞቃዲሾ መረጃ ማጋራቷን አስታውቀዋል።
የአየር ድብደባው የአሜሪካ እና ሶማሊያን ጠንካራ የጸረ ሽብር ትብብር እንደሚያሳይና በትራምፕ የስልጣን ዘመንም ይሄው አጋርነት ይበልጥ እንዲጎለብት ፍላጎታቸው መሆኑንም ነው ያነሱት።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት በበኩላቸው የአየር ጥቃቱ የአይኤስን "የሽብር ጥቃት የማድረስ አቅም ያዳከመ ነው" ያሉ ሲሆን፥ አሜሪካ ሽብርተኞችን አድና በመያዝ እንደምታጠፋ ግልጽ አቋሟን ያሳየችበት ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ የአየር ድብደባው የተፈጸመው በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ ጎሊስ ተራሮች ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የፑንትላንድ መንግስት የአይኤስ "ከፍተኛ አመራሮች በተገደሉበት ጥቃት የተሳተፉ አለማቀፍ አጋሮች" አመስግኗል።
በ2010 መጀመሪያ በሶሪያ እና ኢራቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው አይኤስ በአሜሪካና ሌሎች አጋር ሀገራት በተፈጸመበት ጥቃት አቅሙ ተዳክሞ በአሁኑ ወቅት በዋነናት በአፍሪካ ይንቀሳቀሳል።
የአይኤስ የሶማሊያ ክንፍ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው አልሸባብ በከዱ ታጣቂዎች በፈረንጆቹ 2015 መቋቋሙ ይታወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው አስተዳደር (ባይደን) በአይኤስ ሶማሊያ ላይ ፈጣን እርምጃ አለመውሰዳቸውን ወቅሰው "እኔ ግን አድረግኩት" ሲሉ ራሳቸውን አሞካሽተዋል።
ይሁን እንጂ ባይደን በሰጡት ትዕዛዝ የቡድኑ መሪ ቢላል አል ሱዳኒ እና ሌሎች 10 ከፍተኛ አመራሮች በሰሜናዊ ሶማሊያ በ2023 መገደላቸው የሚታወስ ነው።
በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናችው ማብቂያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ እንዲወጡ ይወሰኑት ትራምፕ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከገቡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሶማሊያ የአየር ጥቃት እንዲፈጸም አዘዋል።