ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ተዋጊዎች "አይኤስ ሶማሊያ"ን እየተቀላቀሉ ነው ተባለ
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአይኤስ የሽብር ቡድን ክንፍ አባላት ቁጥር ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተገልጿል
የመንግስታቱ ድርጅት ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት ቡድኑ በፑንትላንድ ይዞታውን እያስፋፋ መሆኑን አመላክቷል
የአለማቀፉን የሽብር ቡድን አይኤስ የሶማሊያ ክንፍ (አይኤስ ሶማሊያ) የሚቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት ገለጸ።
ድርጅቱ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በቁጥር አነስተኛ አባላት ያሉት ነገር ግን ተጽዕኖው ከፍተኛ የሆነውን ቡድን የውጭ ሀገር ተዋጊዎች በስፋት እየተቀላቀሉት ነው ብሏል።
በሶማሊያ የመንግስታቱ ድርጅት የማዕቀቦች ቁጥጥር ቡድን ያወጣው ሪፖርት "አይኤስ ሶማሊያ" የአባላቱ ቁጥር በእጥፍ አድጎ ከ600 እስከ 700 ደርሷል ነው ያለው።
"የውጭ ሀገር ተዋጊዎች ወደ ፑንትላንድ በባህርና በየብስ እየገቡ ነው" ያለው ሪፖርቱ፥ የተዋጊዎቹ እየተበራከተ መሄድ የቡድኑን አቅም እያጠናከረው እንደሚገኝ አብራርቷል።
በሶማሊያዋ ፑንትላንድ የሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን ከተቀናቃኙና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው አልሸባብ ግዛቶችን በማስለቀቅ እንዲይዝ እንዳደረገው መገለጹንም ቪኦኤ ዘግቧል።
የደህንነት ምንጮች "አይኤስ ሶማሊያ" በፑንትላንድ ካል ሚስካድ ተራራዎች የሚያደርገው እንቅስቃሴ መጠናከርም ስጋት መፍጠሩን አንስተዋል ነው ያለው ዘገባው።
የተመድ ሪፖርት በጥቂቱ የስድስት ሀገራት ተዋጊዎች ቡድኑን በመቀላቀል ላይ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሞሮኮ እና ታንዛኒያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ቡድኑን መቀላቀላቸውንና በቁጥጥር ስር የዋሉ ተዋጊዎች ከመካከለኛው ምስራቅ ከመጡ አሰልጣኞች ጋር እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ሪፖርቱ አመላክቷል።
አሜሪካ፣ ሶማሊያ እና በአፍሪካ የአሜሪካ እዝ የአይኤስ ሶማሊያ ተዋጊዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱንና ከባለፈው አመት በእጥፍ መጨመሩን ባለፈው ወር መግለጻቸው ይታወሳል።
የአይኤስ ሶማሊያ አባላት ቁጥር አነስተኛ ቢመስልም የውጭ ሀገር ተዋጊዎች አሁን በሚታየው ደረጃ እየተቀላቀሉት ከቀጠሉ በቅርብ አመታት ውስጥ ለሶማሊያም ሆነ ለቀጠናው ስጋት መደቀኑ አይቀሬ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ቀንድ የሚታየው ወቅታዊ ውጥረትም የቡድኑን የሰው ሃይል እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ተገምቷል።
አይኤስ አለማቀፍ ተጽዕኖውን ለማሳደግ ዘጠኝ ቀጠናዊ ቢሮዎች (አል ካራር) አሉት። ሶማሊያም በ2022 የቡድኑ ቢሮ የተከፈተባት ሀገር መሆኗ ይነገራል።
የመንግስታቱ ድርጅት ምንም እንኳን በሶማሊያ የአል ካራር ቢሮ አመራሮች ቢገደሉም ጠንካራና ያልተማከለ እንቅስቃሴውን ማስቆም እንዳልተቻለ አምኗል።
ባለፈው አመት ሰኔ ወር ከአሜሪካ የአየር ጥቃት ያመለጠው የአይኤስ ሶማሊያ የቀድሞ መሪ አብዱልቃድር ሙሚን በአፍሪካ የአይኤስ ክንፎች መሪ ሆኖ መሾሙ ተመላክቷል።
አይኤስ ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት በሙሚን የቀድሞው ምክትል አብድራሃማን ፋሂየ ኢሴ እየተመራ እንደሚገኝና የፋይናንስ ጉዳዮችንም አብድዋሊ ዋረን ዋላቅ እንደሚያስተዳድር የተመድ ሪፖርት ጠቁሟል።