በሩሲያ እራሳቸውን የአይኤስ አባል እንደሆኑ የገለጹ ታሳሪዎች የእስርቤቱን ሰራተኞች ማገታቸው ተነገረ
ዛሬ ከሰአት በኋላ ተፈጥሯል በተባለው አደጋ እስካሁን አንድ የእስር ቤት ሰራተኛ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል
በአሁኑ ሰአት የሀገሪቱ ጸጥታ እና የደህንነት ተቋማት ታጋቾችን ማስለቀቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው
በሩሲያ እራሳቸውን የአይኤስ አባል እንደሆኑ የገለጹ ታሳሪዎች የእስርቤቱን ሰራተኞች ማገታቸው ተነገረ።
በሩሲያ ደቡባዊ ቮልጎግራድ ክልል በሚገኝ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ታሳሪዎች የተቋሙን ሰራተኞች ማገታቸው ተሰምቷል፡፡
እራሳቸውን የአይኤስ አባል እንደሆኑ የገለጹት አጋቾቹ እስካሁን አንድ ሰው የገደሉ ሲሆን አራት ሰዎችን ደግሞ አግተው እንደሚገኙ ነው የተዘገበው፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወሩ በሚገኙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሶስት የእስር ቤት ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች በደም ተነክረው መሬት ላይ ወድቀው ታይተዋል፡፡
በዚህም የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይም ሊያሻቅብ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በጥቃቱ ስለት የያዙ አራት ታሳሪዎች መሳተፋቸውን የዘገቡት የሩሲያ መገናኛ ብዙሀን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጥረት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት በጉዳዩ ዙሪያ ከእስር ቤቱ አመራሮች ጋር መመከራቸውን ተናግረዋል፡፡
በሳምንታዊ የብሄራዊ ደህንነት ስብሰባ ላይ እንዳሉ ስለአደጋው የተነገራቸው ፑቲን ሁኔታው በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ተጨማሪ ማብራርያዎችን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች እገታው በፍጥነት እና ሳይታሰብ የተከናወነ መሆኑን ገልጸው ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከደህንነት እና ከሌሎች የጸጥታ አካለት ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
አጋቾቹ እስካሁን የአይኤስ አባል መሆናቸውን ከማሳወቅ በዘለለ እገታውን ለምን እንደፈጸሙት እና ተጨማሪ ፍላጎት እንዳላቸው አላሳወቁም፡፡
በስፍራው በሚገኙ የእስር ቤት ሰራተኞች ተቀርጾ በወጣው አንድ ቪድዮ ላይ ከአጋቾቹ መካከል አንዱ በሙስሊም እስረኞች ላይ የሚፈጸመው በደል እንዳማረራቸው ሲናገር መደመጡን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
ከዩክሬን ጋር እያደረገች ባለችው ጦርነት ላይ ትኩረቷን የሰጠችው ሩሲያ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች እየጎበኟት ነው፡፡
ባሳለፍነው ሰኔ በደቡባዊ ሮስቶቭ ክልል በተመሳሳይ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስድስት እስረኞች የእስር ቤቱን ሰራተኞች አግተው በጸጥታ ሀይሎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
በቮልጎግራድ ክልል የሚገኝው የአሁኑ አደጋ የተከሰተበት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት የወንዶች እስር ቤት 1241 እስረኞች የሚገኙበት ነው፡፡