እስራኤል ከቀይ ባህር አቅጣጫ የተተኮሰ ሚሳኤል አከሸፍኩ አለች
በወደብ ከተማዋ ኢላት ያነጣጠረው ሚሳኤል የእስራኤልን ግዛት ሳያቋርጥ ተመተቶ መውደቁ ተገልጿል
በከተማዋ ተደጋጋሚ የሚሳኤልና ደሮን ጥቃት ያደረሰው የየመኑ ሃውቲ ለዛሬው የጥቃት ሙከራ ሃላፊነት አልወሰደም
እስራኤል ከቀይ ባህር አቅጣጫ የተተኮሰ ሚሳኤል አከሸፍኩ አለች።
የወደብ ከተማዋ ኢላት የጥቃቱ ኢላማ እንደነበረች የተገለፀ ሲሆን ዜጎች ራሳቸውን እንዲያድኑ ዛሬ ጠዋት የማስጠንቀቂያ ድምፅ ተለቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ሚሳኤሉ የእስራኤልን ድንበር ሳያቋርጥ አየር ላይ ተመቶ ወድቋል ነው ያለው የሀገሪቱ ጦር ባወጣው መግለጫ።
ጦሩ የሚሳኤሉ አይነትና የመነሻ ስፍራውን አልገለፀም።
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ በኢላት ከተማ የባለስቲክ ሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት ማድረሱ ከዛሬው የጥቃት ሙከራ ጋር ስሙ እንዲያያዝ አድርጎታል።
እስራኤል በጋዛ የምትፈፅመውን ድብደባ እንድታቆም ማሳሰቡን የቀጠለው ሃውቲ ግን እስካሁን ሃለፊነት አልወሰደም።
በኢራን ድጋፍ እንደሚያገኝ የሚታመነው ሀውቲ በአሜሪካና ብሪታንያ ከ400 በላይ ጥቃቶች ቢፈፀሙበትም አሁንም ድረስ እስራኤልና አጋሮቿን መገዳደሩን ቀጥሏል።
በዚህ ሳምንት የብሪታንያ መርከብ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል፤ የአሜሪካን ድሮንም መትቶ ጥሏል።
ቡድኑ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን "ወረራ" ካላቆመች በቀይ ባህር በሚጓዙ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች ላይ ጥቃቴ ይቀጥላል ብሏል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን የቡድኑን ጥቃት "ግድየለሽ እና ለፍልስጤማውያን እርባና የሌለው" ብሎታል።
የሃውቲዎች እርምጃ ለኢትዮጵያ፣ የመን እና ሱዳን በፍጥነት መድረስ ያለባቸው ሰብአዊ ድጋፎችና መድሃኒቶች ጉዞ እንዲጓተት ማድረጉን ነው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር የተናገሩት።
አሜሪካ በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን እንደምትቀጥል መግለፃቸውንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።